Search

ከታሪክ ተምሮ ነገን የቀደመው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት

ረቡዕ ጥቅምት 04, 2019 129

የዓለም አቀፉ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የደኅንነት ምኅዳር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት እየተቀያየረ ይገኛል። ቋሚ የኃይል አሰላለፎች እየፈረሱ፣ አይገመቴነት የዘመኑ ዋነኛ መገለጫ በሆነበት እና የባለብዙ ዋልታ ዓለም ሥርዓት በሚወለድበት በዚህ ወቅት፣ የሀገራት ሕልውና እና ብሔራዊ ጥቅም የሚረጋገጠው በሚገነቡት ሁለንተናዊ የዝግጁነት አቅም ነው።

በተለይም ምሥራቅ አፍሪካ፣ ቀይ ባሕር እና የሕንድ ውቅያኖስ በሚገናኙበት እንዲሁም የዓለም የነዳጅ እና የንግድ መተላለፊያ በሆነው የባብ አል-መንደብ ስትራቴጂያዊ ቀጣና ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ በአካባቢው የሚነሡ ማናቸውም ጂኦ-ፖለቲካዊ ማዕበሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚነኳት መሆኑ አይቀሬ ነው።

ይህንን ተለዋዋጭ ነባራዊ ሁኔታ በብቃት ለመሻገር እና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር፣ ዘመኑን የዋጀ የመከላከያ እና የደኅንነት ኃይል መገንባት የምርጫ ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ ሆኗል። የኢትዮጵያ የታሪክ ምዕራፎች በግልጽ እንደሚያስረዱት ሀገራችን ወታደራዊ አቅሟን አጠናክራ በተገኘችባቸው ዘመናት የራሷን ጉዳይ በራሷ ከመወሰን ባለፈ የተጽዕኖ አድማሷን እስከ ቀይ ባሕር እና ሕንድ ውቅያኖስ ማስፋት ችላለች።

በአንጻሩ በውስጣዊ ሽኩቻ ተጠምዳ ከዓለም የቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ አብዮቶች ተዘናግታ በቆየችባቸው ወቅቶች፣ የውጭ ኃይሎች በእሷ ላይ የሚወስኑባት እና መውጫ መግቢያ በሯ የሚዘጋባት ሁኔታ ተፈጥሯል።

ከዓድዋ ድል ማግስት የተፈጠረው መዘናጋት በማይጨው ጦርነት ወቅት ያስከፈለው ከባድ ዋጋ ለዚህ ሕያው ማሳያ ነው። በወቅቱ ወራሪው ኃይል ለአራት ዐሥርተ ዓመታት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና በጦር አውሮፕላኖች ተደራጅቶ በሰማይ ሲመጣ፣ ኢትዮጵያ ግን ባልተቀየረ ቁመና እና ወታደራዊ ባልሆኑ ጥቂት አነስተኛ አውሮፕላኖች በምድር ለመግጠም ተገድዳ ነበር።

ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባልተዘጋጁበት ግንባርና ባልተጠበቀ የውጊያ አውድ መገኘት የሚያስከትለውን ታሪካዊ ቁጭት የተገነዘበው የመደመር መንግሥት፣ ይህንን መሻገር ቀዳሚ ኃላፊነት አድርጎ እየሰራ መሆኑን የገለጹት።

የነገውን የውጊያ አውድ ቀድሞ ለመተንበይ፣ ኢትዮጵያ በጸጥታ እና በመከላከያ ዘርፍ ሥር ነቀል ሪፎርሞችን አካሂዳለች። ትናንት በምድር፣ ከትናንት ወዲያ በሰማይ የመጣው የደኅንነት ስጋት፣ ነገ በሳይበር፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎት እና በረቀቁ የቴክኖሎጂ አውዶች ሊመጣ እንደሚችል ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት እያደረገች ትገኛለች። 

በዚህም መሠረት የኢትዮጵያን ታላቅነት፣ የቀጠናውን ወቅታዊ ሁኔታ እና የወደፊቱን የዓለም አካሄድ ያገናዘበ ዘመናዊ፣ ብቁ እና ንቁ የመከላከያ ኃይል የመገንባት ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በተለይም በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባሕር አካባቢ የሚታየውን የኃያላን መራኮት እና የጸጥታ ተለዋዋጭነት በብቃት ለመመከት፣ ኢትዮጵያ በቀጠናው የአየር የበላይነትን ለመፍጠር የሚያስችላትን ስትራቴጂካዊ አቅም በመገንባት ላይ ትገኛለች።

 

የሚገነባው የመከላከያ እና የደኅንነት ሥርዓት ዋነኛ ዓላማ ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት አስቀድሞ በመረጃና በቴክኖሎጂ ማወቅና መግታት ነው። ከዚህ አልፎ ስጋቶች ወደ ተግባር የሚሸጋገሩ ከሆነ በብቃት መከላከል፣ ሁኔታዎች ከባሱም በየትኛውም የውጊያ አውድ ተሰማርቶ በአሸናፊነት መወጣት የሚችል የማይበገር ቁመና መፍጠር መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የተሰጠውን ግዳጅ በላቀ ወታደራዊ ጥበብና በተግባር የመፈጸም አቅም ያለው፣ በጀግንነትና በጽናት ለሀገሩና ለሕዝቡ ክብር ውድ ሕይወቱን ጭምር ዋጋ የሚከፍል የድል ሠራዊት ነው።

እንደ አባቶቹ ሁሉ ድልን መለያውና ልማዱ ያደረገው ይህ ሠራዊት፣ ባለፉት ዓመታት በግንባርም ሆነ በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ አሻጥርም ሆነ በሚዲያ ዘመቻ የተከፈቱ የተቀናጁ ጥቃቶችን በጽናት መክቶና የጠላትን ሴራ በጣጥሶ ሀገርን ማሻገር የቻለው በዚሁ የማይበገር የመፈጸም አቅሙና ጀግንነቱ ነው።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ መልክዓ-ምድርና ፖለቲካ ውስጥ መሪና መልህቅ ሀገር መሆኗን የምታረጋግጠው በማንም ችሮታ ሳይሆን በራሷ ውስጣዊ ጥንካሬና በጀግናው መከላከያ ሠራዊቷ የላቀ ወታደራዊ ቁመና ነው።

ሰላምን በውይይት፣ በድርድርና በሕብረ ብሔራዊ አንድነት የማጽናት ጥረቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የሀገራችንን የባህር በር የማግኘት ፍትሐዊ ፍላጎት፣ የልማት ፕሮጀክቶችን ደኅንነትና ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ ይህ በደምና በአጥንቱ ሀገር የሚያጸናው የድል ሠራዊት ወሳኝ ዋስትና ነው።

ለድርቅ፣ ለጦርነት፣ ለኢኮኖሚያዊ ቀውሶችና ለጂኦ-ፖለቲካዊ ፈተናዎች የማትንበረከክ ትልቅ ሀገር እውን የማድረጉ ጉዞ፣ በዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስ፣ በአየር የበላይነትና ለሀገሩ በጽናት ዋጋ በሚከፍለው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን የላቀ ዝግጁነት ታጅቦ በድል ይቀጥላል።

በበረከት ሽመልስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: