Search

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የቴክኒክ ገምጋሚዎች ቡድን አዲስ አበባ ገባ

ሓሙስ ጥቅምት 05, 2019 43

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የቴክኒክ ገምጋሚዎች ቡድን ኢትዮጵያ የ2028ቱን የአፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ ያለችበትን የዝግጅት አቅም ለመገምገም አዲስ አበባ ገብቷል።

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አክሊሉ ታደሰ (ዶ/ር) ለኢቲቪ እንደገለጹት፣ ቡድኑ በሚኖረው ቆይታ የስፖርት መሠረተ ልማቶችን፣ የስታዲየሞችን ደረጃ፣ የሆቴልና የመስተንግዶ ዘርፎችን እንዲሁም የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ዝግጁነትን በዝርዝር ይገመግማል።

በአዲስ አበባ ከሚያደርገው ምልከታ በተጨማሪ በመላ ሀገሪቱ ተዘዋውሮ የተከናወኑ ሥራዎችንና የልማት እንቅስቃሴዎችን ይመለከታል።

ቡድኑ አስፈላጊውን መረጃ ሰብስቦ ካጠናቀቀ በኋላ የሚያቀርበውን ዝርዝር ሪፖርት መሠረት በማድረግ፣ የውድድሩን አስተናጋጅ ሀገር የመጨረሻ ውሳኔ ለካፍ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሚያስተላልፍ ይሆናል።

ኢትዮጵያ ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በኋላ አህጉራዊውን ውድድር ዳግም ወደ ምድሯ ለመመለስ ጥያቄ ማስገባቷ ይታወሳል።

በይበልጣል ሰውነት

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: