Search

አፍሪካ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ መሆን አለባት፦ የገንዘብ ሚኒስቴር

ሓሙስ ጥቅምት 05, 2019 50

በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና በዓለም ባንክ (World Bank) ዓመታዊ ስብሰባዎች ጎን ለጎን በተካሄደ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ውይይት ላይ ኢትዮጵያ ተሳትፎ አድርጋለች።

በዚሁ መድረክ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ ትዕግሥት ፍስሃ ከዓለም ባንክ፣ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF)፣ ከጌትስ ፋውንዴሽን (Gates Foundation) ከፍተኛ ተወካዮች እና ከተለያዩ ሀገራት ሚኒስትሮች ጋር ፍሬያማ ሀሳቦችን ተለዋውጠዋል።

ውይይቱ ታዳጊ ኢኮኖሚ ያላቸው ሀገራት የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሎጂን ለአካታች ዕድገትና ለዘላቂ ልማት እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ መፍትሔዎችን ለመቀየስ እና የተጨባጭ ትብብር መስኮችን ለመለየት ያለመ ነበር።

በመድረኩ ባደረጉት ንግግር ትዕግሥት ፍስሃ፤ ኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና የሰው ሠራሽ አስተውሎትን (AI) በልማት ስትራቴጂዋ ውስጥ በዋና ማዕከልነት ለማስገባት ቁርጠኛ ውሳኔ ማድረጓን አብራርተዋል።

ለዚህም ማረጋገጫ የሚሆነው ለዘርፉ የተሰጡ ተቋማትን በልዩ ሁኔታ መመስረቷ እንደሆነ የጠቀሱት ሚኒስትር ዲኤታዋ፤ በ2012 ዓ.ም የተቋቋመውን የኢትዮጵያ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት እና በ2018 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ የተመሰረተውን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲን በምሳሌነት አንስተዋል።

በተጨማሪም አፍሪካ ከአፍሪካዊያን ነባራዊ ሁኔታ፣ መረጃዎች እና ቋንቋዎች ጋር የተጣጣሙ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) መፍትሔዎችን የማላመድ፣ የመተግበር እና በሂደትም የማልማት አቅሟን በመገንባት በዘርፉ የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: