Search

የብረት ክንድ እና የአንበሳ ልብ፦ ለጠላቶቿ መቅሰፍት የሆነው የኢትዮጵያ ሠራዊት

ሓሙስ ጥቅምት 05, 2019 39

'ወጥን ማን ያውቀዋል?' ቢሉ፣ 'ቀላዋጭ!' ይላል የሀገሬ ሕዝብ፤ “የኢትዮጵያን ወታደር ማን ያውቀዋል?” ቢሉ ደግሞ፣ “የቀመሰው!” ነው የእኛ መልስ!” ይላሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥልቅ እና ተጨባጭ አባባል፣ የኢትዮጵያን ወታደር ግርማ ሞገስ እና የማይበገር አቅም በአንድ ዓረፍተ ነገር የሚያሳይ ሕያው እውነታ ነው።

የኢትዮጵያ ወታደር ክንድ ጥንካሬ በቃላት ድርሰት የሚገለጽ ሳይሆን በታሪክ ምዕራፎች ውስጥ ጠላቶቹ ላይ ባስመዘገባቸው የውጊያ ውሎዎች ያስመሰከሩት እውነት ነው።

ይህ የአንበሶቹ ክንድ ከዓድዋ እስከ ዛሬዋ ዘመናዊት ኢትዮጵያ ድረስ የሀገራችንን ሉዓላዊነት እና ነፃነት አስከብሮ ያስቀጠለ፣ ለጠላቶች መቅሰፍት፣ ለሕዝቡ ደግሞ ጽኑ መከታ የሆነ ታላቅ የጀግንነት መገለጫ ነው።

በሀገራዊ የኪነ-ጥበብ ሀብታችን ውስጥ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሰው "የኢትዮጵያ ጀግኖች ስማቸው ሲነሳ፤ ከሩቅ ያስፈራሉ እንደ ዱር አንበሳ…" የሚለው ዘመን ተሻጋሪ ዜማ ደግሞ የኢትዮጵያውያንን የጀግንነት ግርማ በጥበብ ያንጸባርቃል።

የኢትዮጵያ ልጆች ጀግንነትን በወሬ የወረሱት ሳይሆን በደም ያገኙት መለያ እሴታቸው ነው። ለሀገራቸው ድንበር እና ክብር ሲባል ዐሥር ሞት ቢኖር እንኳን ራሳቸውን አሳልፈው ለመስጠት የማያመነቱበት ምስጢር በደማቸው ውስጥ ያለው የሀገር ፍቅር ነው።

ይህ እንደ አንበሳ የሚያስፈራ ግርማ ሞገስ ድንበር የሚደፍሩ ጠላቶችን ከሩቅ የሚያርድ፣ የኢትዮጵያን ስም በሚያነሱበት ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንዲያጡ የሚያደርግ የቁርጠኝነት መንፈስ ነው።

የነፃነትን ጣዕም አጥብቀው የሚያውቁት የኢትዮጵያ ልጆች በየትኛውም የከፋ ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ እናታቸውን ለጥቃት አሳልፈው እንደማይሰጡ በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ወቅት አስመስክረዋል።

በአምስቱ ዓመታት የወረራ ዘመን ማዕከላዊ መንግሥት ባይኖርም የዐርበኝነት ወኔ ግን በየጫካው እና በየበረሃው እንደረመጥ ተቀጣጥሎ ጠላትን ቁምስቅል ያሳይ ነበር።

እንደ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ፣ ሌተናል ጄኔራል ጃገማ ኬሎ፣ ኮሎኔል አብዲሳ አጋ እና ራስ አበበ አረጋይ ያሉ የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጆች ዱር ቤቴ ብለው የከፈሉት ውድ መስዋዕትነት፣ የኢትዮጵያ ነፃነት በደም እና በአጥንት የተገነባ መሆኑን ያረጋገጠ ነው።

ወራሪውን በሀገሩ እረፍት ያሳጣው የኮሎኔል አብዲሳ አጋ የጣሊያን በረሃዎች ጀብዱ የኢትዮጵያን ጀግኖች ልብ ከፍታ ያስመሰከረ ነው።

ይህ ወኔ በሀገር ወሰን ብቻ የተገደበ አልነበረም። በኮሪያ ዘመቻ የተሰማራው የቃኘው ሻለቃ፣ በውጭ ሀገር ምድር ላይ አንድም የኢትዮጵያ ወታደር ሳይማረክ እና የሰማዕታት አፅም እንኳን ለጠላት ሳይተው በድል የመመለሱ ገድል፣ የኢትዮጵያ ወታደር ለክብሩ የሚከፍለውን ወደር የሌለው ታማኝነት ያሳያል።

በካራማራ ተራሮች ላይ የታየው ተጋድሎም ኢትዮጵያ በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ብትሆን ድንበሯን የሚያስከብር የብረት ክንድ እንደማታጣ ለዓለም ያስመሰከረ ታሪካዊ ክስተት ነው።

እነዚህ ጀግኖች ያሳዩት ጽናት እና ገድል የትውልድ ቅብብሎሽ መሠረት በመሆን እስከ ዛሬው ዘመን ድረስ በጽኑ መሠረት ላይ ቆሟል።

ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት በደም በተወረሰ ወኔው ላይ ዘመኑን የሚዋጅ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አቅም አክሏል።

ሠራዊታችን በምድር፣ በአየር፣ በባሕር እና በሳይበር ምኅዳሮች የተሟላ ዝግጁነት እና ብቃት ያለው ዘመናዊ የጦር ኃይል ሆኖ ተገንብቷል።

ይኸው በዘመናዊ የጦር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የተደገፈ አቅም ከአያት እና ከአባቶቻችን ከተወረሰው የአንበሳ ልብ ጋር ሲቀናጅ ኢትዮጵያን በክፉ ለሚያስቡ ጠላቶቹ የብረት ክንድ የአንበሳ ልብ ነው።

በወኔ የታጠቀው እና በቴክኖሎጂ የዘመነው መከላከያ ሠራዊታችን የነፃነታችን ዘብ፣ የሕዝባችን ሰላም ዋስትና እና የሀገራችን ታላቅ ኩራት ሆኖ ታሪካዊ ግዴታውን በብቃት እየተወጣ ይገኛል።

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: