ኢትዮጵያ የራሷ የባሕር በር ባለመኖሯ በምርቶች በሎጂስቲክስ፣ በወደብ አገልግሎት እና በወጪ ንግድ ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጫና እያደረሰባት እንደሚገኝ የምጣኔ ሀብት እና የአካዳሚክ ምሁራን ገለጹ።
በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን “ዳጉ” ፕሮግራም ላይ ተገኝተው ማብራሪያ የሰጡት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ሙሉጌታ ተፈራ (ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪው ፕርፌሰር ዓለማየሁ ተክለማርያም እንደገለጹት የባሕር በር ጥያቄ ከምኞት እና ከቁጭት ባለፈ በተጨባጭ መሬት ላይ ሊፈታ የሚገባው መሠረታዊ ጉዳይ ነው ።
ዶክተር ሙሉጌታ የባሕር በር አለመኖር በኢትዮጵያ የገቢ እና ወጪ ንግድ ላይ የፈጠረውን ከፍተኛ የወጪ ጫና አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በሕዝብ ቁጥሯም ሆነ በቆዳ ስፋቷ ግዙፍ በመሆኗ አንድ ወደብ ብቻ ሳይሆን በርካታ የመውጫ እና መግቢያ በሮች እንደሚያስፈልጓትም ጠቁመዋል።
አክለውም የኢኮኖሚ ሁኔታችን በአስተማማኝ ሁኔታ ሲመለስ የፖለቲካው ሁኔታ እንደሚቀየር፣ የዜጎች የኑሮ ጫና ቀልሎ የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር እና ይህም ለሰላም እና ደኅንነትን መረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ተክለማርያም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ከመንግሥት፣ ከምሁራን እና ከዜጎች የሚጠበቁ በርካታ ተግባራት እንዳሉ አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት ምስረታ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ያለ ባሕር በር እውን ሊሆን እንደማይችል እና የባሕር በር ማግኘት የኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ማሳሰባቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ከሁሉም ጎረቤቶቿ ጋር በሰላም፣ በጋራ ጥቅም እና በሰጥቶ መቀበል መርህ አብራ ለመሥራት ዝግጁ መሆኗን እና የቀጣናው ሀገራት በጋራ ተሳስረው እንዲያድጉ ፍላጎት እንዳላትም ተመላክቷል።
ተጋባዦቹ በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ እንዳሰመሩበት በዓለም ላይ እየተካሄደ ያለውን ፈጣን ጂኦፖለቲካዊ ለውጥ ተረድቶ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች በቂ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል።
ብሔራዊ ጥቅማችንን ለድርድር ሳናቀርብ ዲፕሎማሲያችንን በማጠናከር እና የሀገር ውስጥ ሰላምን በማስጠበቅ የኢትዮጵያን የብልፅግና እና የሥልጣኔ ጉዞ ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
#የመደመርመንግሥት #ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ
በሜሮን ንብረት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: