የትግራይ ሕዝብ ከኢትዮጵያዊነቱ ጋር ያለው ታሪካዊ ትስስር ጠንካራ እንደሆነ እና ድምፁ በፖለቲካዊ ምክንያቶች ተገድቦ መቆየቱን የመቐለ ከተማ የቀድሞ ምክትል ከንቲባ አቶ ገብረ ኪሮስ ህሉፍ ገልጸዋል።
ሕዝቡ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ፣ ሕግ እና ሥርዓትን የሚያከብር መሆኑን የጠቀሱት አቶ ገብረ ኪሮስ፤ በአዲግራት፣ በዓድዋ፣ በመቐለ እና በተለያዩ ከተሞች የኢትዮጵያ ባንዲራ መውለብለቡ እና ብሔራዊ መዝሙር መዘመሩ ለዚህ ማሳያ መሆኑን ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
እነዚህ ክስተቶች የሕዝቡን ብሔራዊ ማንነት እና ስሜት የሚያንጸባርቁ እንደሆኑም አስረድተዋል።
ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ በትግራይ የተከሰቱ የፖለቲካ ሁኔታዎችን ያነሱት የቀድሞው ምክትል ከንቲባ፤ ህወሓት ለሰላምና ለውይይት የተሰጠውን ዕድል በተገቢው መንገድ አልተጠቀመበትም ብለዋል።
ድርድርን ለዘላቂ ሰላም ከመጠቀም ይልቅ የፖለቲካ ጊዜ መግዣ እንደሚያደርገው በመግለጽ፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት በተግባር መከበር እንደነበረበት አስገንዝበዋል።
ህወሓት በታጠቀ ትግል የተመሠረተ ድርጅት በመሆኑ፣ የፖለቲካ ባህሉ በውይይት፣ በዴሞክራሲያዊ ፉክክርና በሕግ የበላይነት ላይ ያለውን ክፍተት እንደሚያሳይ አመልክተዋል።
በተለይም የፖለቲካ አለመግባባቶች ወደ ጦርነት መሸጋገራቸው በሕዝቡ ላይ ከባድ ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ማድረሱን ጠቁመዋል።
የሕወሓት አካሄድ ከሥልጣን ፍላጎትና ከተጠያቂነት ለመሸሽ ከማሰብ ጋር የተያያዘ መሆኑን አቶ ገብረ ኪሮስ ገልጸዋል።
ቡድኑ በሥልጣን ለመቆየት ሲል የትግራይን ወጣቶች ወደ ግጭት እየገፋ ይገኛል ሲሉም ከሰዋል።
ይህም የሕዝቡን የሰላም፣ የልማት እና የመደበኛ ሕይወት ፍላጎት የሚጎዳ አካሄድ እንደሆነ አስረድተዋል።
በትግራይ የሚታዩ የመድኃኒት እጥረት፣ ረሃብ እና ሌሎች ማኅበራዊ ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱ የሚያስችለው መንገድ ሰላምን ማስፈን እና የልማት ሥራዎችን ማስቀጠል እንደሆነም አመልክተዋል።
በግጭት የሚያልፈው ጊዜ የሕዝቡን ሀብት፣ የወጣቶችን ዕድል እና የክልሉን የዕድገት አቅም እንደሚጎዳ ተናግረዋል።
ህወሓት ከኤርትራ ጋር ፖለቲካዊ ትስስር እንዳለ የጠቀሱት የቀድሞው ምክትል ከንቲባ፤ ይህ ግንኙነት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እና በትግራይ ሕዝብ የወደፊት ዕድገት ላይ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ መሆኑን ገልጸዋል።
የባሕር በር ጉዳይን በተመለከተ የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት ከብሔራዊ ጥቅም እና ከረጅም ጊዜ ስትራቴጂያዊ አስፈላጊነት ጋር የተያያዘ መሆኑን አስረድተዋል።
ጉዳዩ በሰላማዊ እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍትሔ ሊያገኝ እንደሚገባም ገልጸዋል። የባሕር በር ጥያቄን የሚቃወሙ አካላትን በመተቸት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ከድርጅታዊ ወይም ከፖለቲካዊ ፍላጎት በላይ መታየት እንዳለበት አበክረው ተናግረዋል።
አቶ ገብረ ኪሮስ በቆይታቸው የትግራይ ሕዝብ የሰላም፣ የልማት እና የሀገራዊ ተሳትፎ ፍላጎት እንዲከበር እንዲሁም የፖለቲካ አለመግባባቶች በውይይት እና በሕጋዊ ሥርዓት እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።
የሕዝቡ ድምፅ በነፃነት እንዲሰማ፣ ወጣቶች ለግጭት ከመጋለጥ ይልቅ በልማት እና በሀገር ግንባታ ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ እና ዘላቂ ሰላምን ማስፈን የጋራ ትኩረት ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: