Search

የ30 ዓመታት የታሪክ ስህተትን የማረም እና የአገራዊ ሕልውና ግዴታ፦ የኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር የመመለስ ፋይዳ

ሓሙስ ጥቅምት 05, 2019 55

የኢትዮጵያ እና የባሕር በር ቁርኝት ጥንታዊውን የአክሱም ሥልጣኔና የታሪክ አዱሊስ ወደብን መሠረት ያደረገ ቢሆንም፤ ላፉት ሦስት አሥርታት ወደብ አልባ ሆና እንድትቀር የተደረገችበት ሁኔታ በጥንታዊ ታሪኳ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅና በቅርብ ዘመን በተፈጸሙ የፖለቲካ ውሳኔዎች የተጫነባት የታሪክ ጠባሳ ነው።

በ1983 ዓ.ም የኤርትራን መገንጠል ተከትሎ በ1985 ዓ.ም የተካሄደውን ህዝበ ውሳኔ እንደ አጋጣሚ በመጠቀም የውጭ ኃይሎችና የታሪክ ጠላቶች የሸረቡት ሴራ ኢትዮጵያን ያለ ምንም የባሕር በር ያስቀራት ክፉ አጋጣሚ ነው።

በተለይም ግብፅን ጨምሮ በርካታ የዓረብ ሀገራት የታጠቁ ንቅናቄዎችን በፋይናንስና በዲፕሎማሲ በመደገፍ ደካማና ከባሕር የተገፋች ኢትዮጵያን የመፍጠር የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ ስሌታቸውን ሲያሳኩ ቆይተዋል።

ይህ የታሪክ ስህተት ላፉት ሦስት አሥርታት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ ደህንነት እና ወታደራዊ ጥንካሬ ላይ ከፍተኛ አደጋ ሲደቅን መቆየቱ ተመላክቷል።

በአሁኑ ወቅት የቀይ ባሕር የንግድ መስመር በሁቲዎች ጥቃት፣ በባሕር ላይ ወንብድና እና በጂኦፖለቲካዊ ፉክክር ምክንያት አስከፊ ደረጃ ላይ የወደቀ ሲሆን፤ ግዙፏና ዋነኛዋ ባለድርሻ ሀገር ኢትዮጵያ ሳትካተትበት ቀጠናውን ለመምራት መሞከር መዋቅራዊ ስህተት መሆኑ ተጠቅሷል።

በአራተኛው ዓመታዊ የቀይ ባሕርና የኤደን ባሕረ-ሰላጤ የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የኢፌዲሪ የባሕር ኃይል አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ እንደገለጹት “የኢትዮጵያ የባሕር ኃይልና የባሕር በር ሚና የመላው ቀጣናውን የጋራ ጥቅም የሚያስከብር” ነው።

ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጋር ያላት ታሪካዊና ስትራቴጂካዊ ቁርኝት በቀጣናው ደህንነት ላይ ሙሉ ባለድርሻ እንድትሆን የሚያደርጋት ባለሙሉ መብት ባለቤት ነች።

ደግሞም በቀይ ባሕር መረጋጋት ላይ ከፍተኛ ፍላጎት ካላቸው ሀገራት መካከል የውጭ ንግዳቸው በየዕለቱ በዚሁ መስመር ከሚያሳልፉ ሀገራት ዝርዝር አናት ውስጥ ኢትዮጵያ ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር የመመለስ ጥያቄ የቅንጦት ወይም የፖለቲካ ፍላጎት ሳይሆን፤ የ30 ዓመታት የታሪክ ስህተትን የማረም፣ የሀገራችንን የኢኮኖሚ ሕልውና የማረጋገጥና የትውልድን ደህንነት የመጠበቅ አገራዊ ጥያቄ ነው።

ኢትዮጵያ ወደ ባሕር በር ስትመለስ የውጭ ንግዷ በአንድ መስመር ላይ ጥገኛ መሆኑ የሚቆም፣ የትራንዚትና የሎጂስቲክስ ወጪዋ የሚቀንስ ሲሆን፤ የጎረቤት ሀገራት ወደቦችም ከኢትዮጵያ ግዙፍ ገበያ በሚያገኙት ፍሰት አብረው የሚያልሙ ይሆናል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር የመመለስ አገራዊ ጉዞ የታሪክ፣ የጂኦግራፊና የኢኮኖሚ ግዴታ ሲሆን፤ የዛሬው ትውልድ በሕግ፣ በሰላማዊ ዲፕሎማሲና በሰጥቶ መቀበል መርህ የባሕር በር ባለቤትነቱን የማረጋገጥ ታሪካዊና ሞራላዊ ኃላፊነቱን የመወጣት ጉዞውን ቀጥሏል።

#የመደመርመንግሥት #MedemerGovernment

በሰለሞን ገዳ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: