Search

የዘመኑ ዓድዋ እና ዐርበኝነት፦ ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

ሓሙስ ጥቅምት 05, 2019 65

የትናንትናው የዓድዋ ዕሴት በታሪክ ማኅደር ውስጥ ተወስኖ የሚቀር ትውስታ ብቻ ሳይሆን፣ የዛሬውን እና የነገውን የሀገር ግንባታ የምንመዝንበት ነው። ይህ ታላቅ መንፈስ ኢትዮጵያዊነትን በከፍታ ላይ ሲያስቀምጥ፣ ጠባብ የቡድንተኝነት እሳቤዎችን እና ከፋፋይ የፖለቲካ አካሄዶችን አጥብቆ ይሞግታል።

በዘመናችን የዓድዋን አስተምህሮ መረዳት ማለት ከግጭት እና ከጦርነት ትርክት ወጥቶ ለሰላም፣ ለዕውቀት እና ለሞራል ልዕልና መገዛት ማለት ነው። ዛሬ ላይ እውነተኛው ዐርበኝነት የሚለካውም በነውጥ ጩኸት ሳይሆን፣ አብሮነትን በማጽናት እና የሕዝብን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ነው።

ኢትዮጵያዊነት በዚህ የዘመናችን ዓድዋ እና ዐርበኝነት ሚዛን ሲታይ በትዕግሥት፣ በአርቆ አስተዋይነት እና በላብ የሚገነባ ዘመን ተሻጋሪ ማንነት ነው። ይህ የኢትዮጵያዊነት ልዕልና እና ትልቅነት ከድንበራችን አልፎ ለዓለም ጭቁን ሕዝቦች የነፃነት እና የእኩልነት ተምሳሌት መሆኑ የታሪክ ሐቅ ነው።

አፍሪካ አሜሪካዊው ሮበርት አሌክሳንደር ያንግ ምዕራባውያን የሰብዓዊ መብት ድንጋጌን ከማርቀቃቸው ከአንድ ክፍለ ዘመን በፊት፣ እ.አ.አ በ1829 ዓ.ም "የኢትዮጵያ ማኒፌስቶ" (The Ethiopian Manifesto) በተሰኘው ጽሑፉ፣ የጥቁር ሕዝቦችን ዓለም አቀፋዊ ነፃነት እና ሰብዓዊ ክብር ሲጠይቅ፣ ኢትዮጵያን የነፃነት ማዕከል አድርጎ ነበር።

ያ በሐሳብ ደረጃ የተነሣው የእኩልነት እና የነፃነት ጥሪ በኢትዮጵያውያን ተጋድሎ ዕውን ሆኗል። ዛሬ በፍጥነት በሚለዋወጠው እና ውስብስብ በሆነው የዓለም ጂኦ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምሕዳር ውስጥ፣ የዚህን "የኢትዮጵያ ማኒፌስቶ" መንፈስ በአዲስ መልክ ማሳደግ የዘመኑ ትውልድ ኃላፊነት ነው።

ቀደምት አባቶቻችን የዓለም ጥቁር ሕዝቦችን የነፃነት ቁጭት በሉዓላዊነት እንዳረጋገጡት ሁሉ፣ የዛሬው ትውልድ ደግሞ ያንን ክብር በኢኮኖሚያዊ ልዕልና፣ በቴክኖሎጂ እና በብልጽግና የማስዋብ የታሪክ አደራ አለበት።

#ትልቅሕዝብ፣ #ትልቅሀገር እና #ታላቅርዕይ ይህንን ይጠይቃሉ። የቀደምት ዐርበኞቻችን ርዕይ የሀገርን ዳር ድንበር ከማስከበር ባለፈ ኢትዮጵያ ከዓለም ጋር የምትገናኝበትን የባሕር በር የማረጋገጥ ሰፊ የዲፕሎማሲ ግብን ያካተተ ነበር። ይሁንና በሂደት በተፈጠሩ ጊዜያዊ የፖለቲካ ሴራዎች እና ሀገራዊ ጥቅምን ባልዋጁ አስተሳሰቦች የተነሣ፣ ይህንን ስትራቴጂያዊ መብታችንን ለማጣት ተገድደናል።

የዘመኑ ዐርበኝነት እዚህ ላይ ነው ትልቁን ሚና የሚጫወተው፤ ከዕለታዊ የፖለቲካ ትርፍ ይልቅ ለሀገር ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅም መቆም። የ130 ሚሊዮን ሕዝብ የኢኮኖሚ ጥማት የሚረካው እና ዕጣ ፋንታው የሚያብበው፣ ሀገራችን ከጂኦግራፊያዊ እስር ስትላቀቅ ነው። ስለሆነም የባሕር በር ጥያቄያችን፣ የታሪክ እና የፍትሕ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የትውልድ ሕልውና ጉዳይ መሆኑን በጥልቀት መገንዘብ ያስፈልጋል።

ይህንን ታላቅ ሀገራዊ ርዕይ ዕውን ለማድረግ በምናደርገው ጉዞ፣ ለባዕዳን አጀንዳ መገዛትን እና ቅጥረኝነትን በጽኑ መታገል የግድ ይላል። ብሔራዊ ክብሩን ለጊዜያዊ ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ የፖለቲካ ነጋዴ የኢትዮጵያን የዕድገት ግስጋሴ ሊያደናቅፍ አይችልም።

አሮጌ እና የቆሙ አስተሳሰቦች አዲስ እና ተራማጅ ሐሳቦችን ለማስተናገድ ሲቸገሩ መታየቱ ተፈጥሯዊ ቢሆንም፣ የዘመኑ ትውልድ ግን ወደ ኋላ ለሚጎትቱ ኃይሎች ጊዜ ሳይሰጥ በምክንያታዊነት እና በዕውቀት ወደ ፊት መሻገር አለበት። የሥልጣኔ እና የዘመናዊነት ሐሳቦችን የሚገፉ ወገኖችን በትዕግሥት እና በሐሳብ ልዕልና እያረሙ፣ ለአዲስ ብሩህ ዘመን በር መክፈት ያስፈልጋል።

በየምሽጉ የሀገርን ዳር ድንበር ከሚጠብቀው የመከላከያ ሠራዊት አንሥቶ በየመስኩ እስከተሰማራው ዜጋ ድረስ፣ የዘመኑ የዐርበኝነት ጥሪ በመደመር ኢትዮጵያን በሥራ እና በጥበብ ማጽናት ነው። የሐሳብ ትግሉን አጠናክረን፣ ብሔራዊ ጥቅማችንን አስቀድመን ከተጓዝን፣ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ዳግም የምትገለጥበት እና የምታበራበት ዘመን ሩቅ አይሆንም።

#የመደመርመንግሥት

በበረከት ሽመልስ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: