የኢትዮጵያን የነገ ገጽታ የመቅረጽ፣ የልማት ምዕራፏን ከፍ የማድረግ እና የትውልድን አደራ የመወጣት ታላቁ ኃላፊነት የዛሬው ወጣት ትከሻ ላይ ያርፋል።
ሀገራችን በጽኑ መሠረት ላይ የተገነባች፣ የበለጸገች እና የተከበረች እንድትሆን በሚደረገው ጥረት የወጣቱ ትውልድ ከጊዜያዊ ስሜት ወጥቶ በዕውቀት እና በሁለንተናዊ ዕይታ ነገን አልሞ መሥራት ይጠበቅበታል።
ይህም ማለት የዛሬውን ፈተና አልፎ የነገውን ታላቅ ስኬት በግልጽ ማየት፣ ለአጭር ጊዜ ጥቅም ሳይሆን ለዘላቂ ዕድገት መቆም እንዲሁም የትናንት ጥላቻዎችን ተሻግሮ የጋራ የወደፊት ተስፋን መገንባት ነው።
ለዚህ ስኬት መሠረት ለመጣል፣ "ወጣቶችን ከዕድገት ጉዞ ለይቶ ማየት አይቻልም፤ የመደመር መንግሥት የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እና የአመራርነት ሚና ለማጠናከር በትኩረት እና በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ይህ አቅጣጫ ወጣቱ ዘመኑን የሚመጥን ክህሎት እንዲኖረው፣ በኢኮኖሚው ውስጥ ተወዳዳሪ እንዲሆን እና የነገ ዕጣ ፈንታን በብቃት እንዲመራ ሰፊ ዕድል ፈጥሯል።
በዘመናዊው ዓለም የነገ ዕይታ በተግባር የሚገለጸው በዕውቀት እና በቴክኖሎጂ አቅም ነው።
ዓለም በፈጣን የዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ በሚጓዝበት በዚህ ወቅት የወጣቱን አቅም የመገንባቱ ራዕይ አንዱ ማሳያ የ "5 ሚሊዮን ኮደርስ" ኢኒሼቲቭ ነው።
በዲጂታል ስትራቴጂ ማዕቀፍ ውስጥ የተጀመረው ይህ ግዙፍ መርሐ ግብር ሚሊዮኖችን በኮዲንግ፣ በዌብ እና ሞባይል መተግበሪያዎች ዝግጅት፣ በዳታ ሳይንስ እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) መሠረታዊ ክህሎቶች ለማሰልጠን ያለመ ነው።
ወጣቱ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለቤት እንዲሆን እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በነጻ ሥራ እና በዲጂታል ዘርፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን ትልቅ መሠረት እየጣለ ይገኛል።
ከዚህ ጎን ለጎን፣ ኅብረብሔራዊ አንድነትን እና ወንድማማችነትን ማጠናከር የሰላም እና የዕድገት ዋና ማረጋገጫ ነው።
ክፍፍልን የሚፈጥሩ አመለካከቶችን በመተው የጋራ እሴቶችን እና የታሪክ ታላቅነትን ማስቀደም ይገባል።
አስተዋይ ወጣት ልዩነቶችን እንደ ውበት እና እንደ ሀብት እንጂ እንደ ግጭት መንስኤ አያይም።
አብሮነት፣ ውይይት እና መቻቻልን መሠረት ያደረገ ሀገራዊ መግባባት ሲፈጠር ብቻ ዘላቂ ሰላም እና ልማት ማረጋገጥ ይቻላል።
በሥራ ወዳድነት እና በኢኮኖሚ ጥንካሬ ላይ ማተኮር ወሳኝ ነው። የነገዋ የተስፋ ምድር የምትገነባው በባዶ ምኞት ሳይሆን በላብ፣ በጥረት እና በጠንካራ የሥራ ባህል ነው።
በግብርናው፣ በኢንዱስትሪው፣ በቱሪዝም እና በኮሪደር ልማት የሚታዩትን ግዙፍ የእድገት እንቅስቃሴዎች እንዲሁም የታላቁ የሕዳሴ ግድብን መሰረታዊ የኃይል እና የልማት አቅሞች እንደ ትልቅ ዕድል በመጠቀም ወጣቱ በሥራ ፈጣሪነት የተሰማራ ባለቤት መሆን አለበት።
ይህ ጉዞ የዛሬ ጥረት ውጤት ነው። ወጣቱ ትውልድ ታሪክን ከመውቅስ ወጥቶ ታሪክ የሚሠራ፣ ችግሮች ሲገጥሙት ከመሸሽ ይልቅ መፍትሔ የሚያመጣ እና ለነገው ትውልድ ጽኑ መሠረት የሚጥል ሊሆን ይገባል።
አርቆ አሳቢነት፣ ፍቅር እና ቁርጠኝነት የተላበሰ ወጣት ሲኖር የተያዘው የብልጽግና ህልም በፅኑ መሠረት ላይ ይቆማል፤ ብሩህ ተስፋውም እውን ይሆናል።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: