አዲስ አበባ እንደ ስሟ ራሷን እያደሰች ዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን፣ የዓለም መሪዎችን እንዲሁም ታዋቂ የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን ማስደመሟን ቀጥላለች።
ከደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ እስከ የጋና እና ኬንያ የሕግ አውጪ ምክር ቤቶች አባላት፣ ከታዋቂው አሜሪካዊ አይ ሾው ስፒድ (IShowSpeed) እስከ የተባበሩት አረብ ኢምሬቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ኻሊድ አል አሜሪ የመዲናዋን የልማት ሥራዎችና ታሪካዊ ቅርሶች ማድነቃቸውን ቀጥለዋል።
በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ከ16 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ያሉት ታዋቂው የተባበሩት አረብ ኢምሬት ተወላጅ ኻሊድ አል አሜሪ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ባደረገው ቆይታ፣ በአዲስ አበባ የሚገኘውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ እና ሐረርን ጎብኝቷል።
ኻሊድ አል አሜሪ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ጉብኝት ካደረገ በኋላ በሰጠው አስተያየት፣ በጉብኝቱ የኢትዮጵያውያንን የማይበገር ጽናትና የአንድነት ምስጢር ተረድቻለሁ ብሏል። በዓድዋ ድል መታሰቢያ ያደረገው ቆይታ "እጅግ አስደናቂ እና ሊረሳ የማይችል ተሞክሮ" እንደሆነም ገልጿል።
በጉብኝቱ ኢትዮጵያውያን በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በማለፍ ያዳበሩትን ጽናት፣ ጥንካሬ እና ተስፋ ያለመቁረጥ መንፈስ መገንዘቡን እና ከዚህም ትምህርት ማግኘቱን ተናግሯል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ብቸኛ ሀገር መሆኗን አውቃለሁ፤ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ደግሞ ከዚህ ጀርባ ያለውን ምስጢር የሚገልጥ የጀግንነት ታሪክ ነው ብሏል።
በዓድዋ ተራሮች 100 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵውያን አርበኞች በአንድነት በንጉሣቸው በአጼ ምኒልክ መሪነት ወራሪውን የፋሺስት ጣሊያን ጦር ድል አድርገዋል። ይህም ኢትዮጵያውያን አፍሪካን ለመቀራመት አሰፍስፈው ለነበሩ ቅኝ ገዢዎች “አንገዛም!” በማለት በቁርጠኝነት የተጋደሉበት ታሪካዊ ክስተት ነው ብሏል ኻሊድ አል አሜሪ።
በዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚገኙት የጀግኖች ኢትዮጵያውያን ሐውልቶችና ምስሎች ሕዝቡ “ከተባበርን እንቆማለን፣ ከተለያየን እንወድቃለን” በሚለው ብሂል መሠረት ጠላትን ለመመከት ተባብሮ በአንድነት መቆሙን የሚያሳዩ ናቸውም ብሏል።
በመካከለኛው ምስራቅና በተባበሩት አረብ ኢምሬት ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው ኻሊድ አል አሜሪ፣ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ሁሉ ይህን ታላቅ ታሪካዊ ስፍራ እንዲጎበኙ መልዕክት አስተላልፏል።
እንደ ኻሊድ አል አሜሪ ያሉ ሚሊዮኖች የሚከታተሏቸው ታዋቂ ሰዎች ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውና ያዩትንም በማኅበራዊ ሚዲያ ለመላው ዓለም ማሰራጨታቸው የሀገራችንን በጎ ገጽታ በማጉላት የቱሪስት ፍሰትን ብሎም የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ የሚያሳድግ ወርቃማ ዕድል ነው።
በላሉ ኢታላ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: