ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ እና በብሔራዊ ጥቅሟ ላይ የተቃጣውን ታሪካዊ የጂኦ-ፖለቲካዊ ከበባ በመመከት፣ የቀጣናውን ልማትና ትስስር ወደ አዲስ የእድገት ምዕራፍ የሚያሸጋግር እውነተኛ ጥንካሬዋንና አንድነቷን በተግባር እያረጋገጠች ትገኛለች።
ለዘመናት ሀገራችንን ሰላሟን እንዳታገኝ ለማድረግ የተሸረቡ ድብቅ ሴራዎች በኢትዮጵያውያን ጽናትና በሀገር መከላከያ ሠራዊታችን ጠንካራ ምላሽ እየተመከቱ ይገኛሉ።
ግብጽ የዓባይን ወንዝ በብቸኝነት የመጠቀም ስግብግብ ፍላጎቷን ለማሳካትና በቀጣናው የበላይ ሆኖ ለመቀጠል በሚል በሐሰተኛ ትርክት ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ጫናዎችን፣ ሀገር የማጥላላት የሚዲያ ዘመቻዎችን እንዲሁም የውክልና ተዋጊዎችን በበጀት እና በሎጀስቲክስ በመደገፍ ኢትዮጵያን በጂኦ-ፖለቲካ ለማጠር ያደረገችው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።
ይልቁንም ግብፅ በቂ የከርሰ-ምድር ውኃ እያላት የኢትዮጵያውያንን የልማት ሕልም ለማደናቀፍ ጽንፈኛ ኃይሎችን በማደራጀት፣ እርስ በእርስ ለማጋጨትና ሀገር አፍራሽ ኃይሎችን በመጠቀም የፈጸመችው እኩይ ተግባር በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ አግባብነት የሌለው ፖለቲካዊ ሴራ መሆኑ ታውቆበታል።
ኢትዮጵያ በበኩሏ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን አጠናቅቃ ኃይል ማመንጨት በመጀመር እና ቀጣናውን በኃይል በማስተሳሰር፣ ግድቡ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አለማድረሱን በተግባር አስመስክራለች።
ይህ ስኬት የካይሮን ሐሰተኛ ክስና ጩኸት ዋጋ ያሳጣው ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የትኛውንም ሀገር ብሔራዊ ጥቅም ሳትነካ በወንድማማችነት መርህ በተፈጥሮ ሀብቷ ተጠቅማ ዜጎቿን ከድህነት የማላቀቅና በብሪክስ (BRICS) ጨምሮ በዓለም አቀፍ መድረኮች በትብብር የመሥራት ጽኑ አቋሟን አሳይታለች።
ከዚህም በላይ በውክልና ጦርነትና በድንበር ትንኮሳ ልትበገር ያልቻለችው ኢትዮጵያ የሕዳሴውን ግድብ ማጠናቀቋን ተከትሎ፣ በኢ-ፍትሐዊ መንገድ ያጣችውን የባሕር በር በሰላማዊና ፍትሐዊ መንገድ ለመመለስ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍታ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ትገኛለች።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሰላማዊ የባሕር በር የማግኘት ጥረቷን እየደገፈው የሚገኝ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ያላትን የማይናወጥ ሕዝባዊ አንድነት፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ የዲፕሎማሲ ተፅዕኖ እና ጠንካራ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አስተባብራ የመመከት ሙሉ አቅም አላት።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ማንኛውንም የውጭ ጫና፣ የጂኦ-ፖለቲካዊ ከበባና የውክልና ትንኮሳ በማክሸፍ ብሔራዊ ጥቅሟን የማስከበር፣ የባሕር በሯን የመመለስና የብልፅግና ጉዞዋን እውን የማድረግ ብቃት ያላት መሆኗን ደጋግማ አስመስክራለች።
#የመደመርመንግሥት
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: