ኢትዮጵያ ቀን ቆርጣ፣ ግልጽ ራዕይ ሰንቃ በፈረንጆቹ 2030 የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለመሆን በትጋት ላይ ትገኛለች። በመደመር ዕሳቤ እና እቅድ የሀገራችንን እምቅ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ኃይል በመጠቀም፣ በዐሥር ዓመት ውስጥ መካከለኛ ገቢ ያላት ሀገር የመፍጠር ግብ ተይዞ በስፋት እየተሰራ ይገኛል።
የዚህች ታላቅ ሀገር ብልጽግና እውን ይሆን ዘንድ በኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች የተጀመሩት አጠቃላይ የማሻሻያ ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ስኬቶችን እያስመዘገቡ ይገኛሉ።
ይህ የሀገር ግንባታ ሂደት ኢኮኖሚያችንን ለአፍሪካ ተምሳሌት የሚያደርግ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመወዳደር የሚያስችል እና ሁለንተናዊ የብልጽግና ዓምዶች የተሟሉለት ማኅበረሰብ ለመገንባት ያለመ ነው።
የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያን የደስተኛ እና የበለጸገ ማኅበረሰብ መኖሪያ ለማድረግ ትልቅ ራዕይ ሰንቆ በፅናት እየሰራ ይገኛል። ይህ ታላቅ ራዕይ የጥቂቶች ሳይሆን የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የጋራ ዓላማ እንዲሆን ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያውያን በታሪካችን ውስጥ በጦርነትና ግጭት፣ በከፋ ረሃብ እንዲሁም በስደትና ጉስቁልና ውስጥ አልፈናል። መከራና ችግር በብዙ ቢፈትነንም ሳንረታና በጽናት ዛሬን አይተናል።
በእነዚህ ሁሉ ፈተናዎች ውስጥ አጽንቶ ያቆየን እና ያበረታን ታላቁ ሀገራዊ ወረት ከአባቶቻችን የወረስነው የአርበኝነት መንፈስ እና ጠንካራ ማኅበራዊ እሴቶቻችን ናቸው።
ዛሬ እነዚህን እሴቶቻችንን መሠረት በማድረግ፣ አንገታችንን ያስደፋንን ድህነት አራግፈን፣ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ በጋራ ቆመናል።
በዚህም ከውጭም ሆነ ከሀገር ውስጥ የሚመጡ ተግዳሮቶችን እና መሰናክሎችን በጥበብ፣ በአንድነት እና በትጋት በመሻገር የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ማድረግ እንችላለን።
በየዘመናቱ በመንገዳችን የተጋረጡብን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ከመንገድ እንዳላስቀሩን ሁሉ ዛሬም ከእንቅልፍ አልባ ጠላቶቻችን ያለማቋረጥ የሚወረወሩብን ፍላጻዎች ከግባችን አያሰናክሉንም፡፡
ከትናንት ተግዳሮት ተምረን፣ ዛሬን በትጋትና በጥበብ ሠርተን ለቀጣዩ ትውልድ የበለጸገችና የተከበረች ሀገር የማሻገር ራዕያችን በተባበረ ክንድ እውን ይሆናል።
በዓይናለም ሃድራ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: