Search

"ዓባይ እና ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቶች ናቸው" - አረጋዊ በርኸ (ዶ/ር)

ቅዳሜ ጥቅምት 07, 2019 44
የናይል እና ቀይ ባሕር ስትራቴጂክ ፎረም፣ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር እና በዓባይ ያላትን ብሔራዊ ጥቅም በሚመለከት ውይይት እያደረገ ነው።
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሕዝብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት እየተደረገ ባለው በዚህ ውይይት ላይ በርካታ ምሁራን በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
የጽሕፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርኸ (ዶ/ር) ዓባይ እና ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቶች መሆናቸውን በዚሁ መድረክ ላይ ገልጸዋል።
ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አቅሟ፣ የጸጥታ እና ደኅንነት መጠበቂያዋ የተፈጥሮ ሀብቷ ሆኖ መቆየቱንም አብራርተዋል።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን ታሪክ እና ሕጋዊ መብት ባልተገነዘቡ፣ ለዘላቂ ጥቅሟ ባልተጨነቁ ኃይሎች ከባሕር በሩ ተገፍታ እንድትቆይ መደረጉን ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ያላት ብሔራዊ ጥቅም ጊዜ የፈጠራቸው ጠላቶች ሊቀይሩት የማይችሉት ነባራዊ ሐቅ በመሆኑ፣ ይህንን እውነት፣ ታሪክ እና ዓለም አቀፍ ሕጎችን መሠረት በማድረግ የባሕር በር እንድታገኝ እና በቀይ ባሕር ያላት ብሔራዊ ጥቅም እንዲከበር ሁሉም ዜጋ መጣር እንዳለበት አሳስበዋል።
በመድረኩ የናይል እና ቀይ ባሕር ስትራቴጂክ ፎረም ኢትዮጵያ በዓባይ እና በቀይ ባሕር ያላት ፍላጎት እና ጥቅም ላይ ያተኮሩ ሐሳቦች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛል።
በባዬ ሙላት

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: