Search

የሀገር ሉዓላዊነትን ማስከበር እና የሕዝብን ሰላም ማረጋገጥ የጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን የማይቀለበስ ቃል ኪዳን ነው

ቅዳሜ ጥቅምት 07, 2019 50

ዛሬ በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን ያለውን ጥልቅ አጋርነት እና አክብሮት ገልጿል።

በጎንደር ከተማ፣ በደባርቅ፣ በወልዲያ፣ በፍላቂት ገረገራ፣ በመቄት፣ በሰቆጣ፣ በወረታ፣ በደብረ ታቦር እና ሌሎች በርካታ ከተሞች የተሰበሰበው ሕዝብ፣ ሠራዊታችን የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበር እያደረገ ላለው ታላቅ ተጋድሎ እና ሕግ የማስከበር አመርቂ ውጤቶች ያለውን ሙሉ ድጋፍ በታላቅ ወኔ ገልጿል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙ እናቶች፣ አባቶች፣ ወጣቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች “የኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት እና እኅታማችነት አርማ የሆነውን የሀገር መከላከያ ሠራዊታችንን እንደግፋለን!” የሚል ሀገራዊ መልዕክት አስተጋብተዋል።

ሕዝቡ በኅብረት ድምፁን ከፍ አድርጎ እንደገለጸው፣ የመከላከያ ሠራዊታችን፣ የፌዴራል እና የክልል የፀጥታ ኃይሎቻችን ለሀገር ሰላም እና ሕልውና የከፈሉት መሥዋዕትነት ሁልጊዜም በወርቃማ ታሪካችን ውስጥ ከፍ ያለ ክብር የሚሰጠው ነው።

በሰልፉ ላይ የተላለፉት መልዕክቶችም የሀገራችንን የወደፊት ብሩህ ተስፋ እና የማይታጠፍ ራዕይ ግልጽ አድርገው ያሳዩ ናቸው። “ከግድቡ ወደ ወደቡ እንሸጋገራለን! የባሕር በር ባለቤትነታችን በልጆቿ መሥዋዕትነት እውን ይሆናል!” በሚሉ መፈክሮች የኢትዮጵያ ታሪካዊ የመልማት እና የታላቅነት ፍላጎት በጎላ ድምፅ ተንጸባርቋል።

የሀገራችንን ሰላም ለማወክ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር የተሰለፉ ኃይሎችን በጽኑ ያወገዙት ሰልፈኞቹ፣ የኢትዮጵያ አንድነት እና እድገት በፀረ-ሰላም ኃይሎች ሴራ በጭራሽ እንደማይደናቀፍ አረጋግጠዋል።

“ለድል የተወለደው መከላከያ ሠራዊታችን አለኝታችን ነው!” በማለት ሀገርን ለማጽናት እና ለማበልጸግ ከመንግሥት ጎን በጽናት እንደሚቆሙ የገለጹት የክልሉ ነዋሪዎች፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በጀግኖች ልጆቿ ክንድ ሁልጊዜም ከፍ ብሎ እንደሚውለበለብ አበብስረዋል።

ይህ ሕዝባዊ ደጋፍ እና አንድነት፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ የማትሸነፍ እና የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ በድል የምታጠናቅቅ መሆኗን የሚያረጋግጥ ነው።

በዮናስ በድሉ

#የመደመርመንግሥት

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: