የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሀገራችንን ሉዓላዊነት፣ የሕዝቧን ሰላም እና ደኅንነት የማስከበር ታሪካዊ እና እንከን-የለሽ ኃላፊነቱን በጽናት እየተወጣ የሚገኝ የሀገር የቁርጥ ቀን ልጅ ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ አያሌ ፈተናዎችን አልፋ፣ በነጻነቷ እና በሉዓላዊነቷ ኩሩ ሆና ለመቆሟ ዋናው መሠረትም የሠራዊታችን የማይናወጥ ክንድ እና መሥዋዕትነት ነው።
ሠራዊታችን ሀገርን የማፍረስ እኩይ ዓላማ ያላቸውን የውስጥ እና የውጭ ጠላቶች ሴራ በማክሸፍ፣ የዜጎችን ደኅንነት በመጠበቅ እና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በመጠበቅ ረገድ ያበረከተው አስተዋጽኦ ወደር የለውም።
የሀገርን ድንበር ከመጠበቅ አልፎ በልማት፣ በሰብአዊ ዕርዳታ አቅርቦት እና በተፈጥሮ አደጋዎች ጊዜ ደራሽ በመሆን የሕዝብ ልጅነቱን በተግባር አሳይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ስለ ሠራዊታችን ጥንካሬ ሲናገሩ፦ “መከላከያ ሠራዊታችን የኢትዮጵያ የነጻነት፣ የክብር እና የሉዓላዊነት የጽናት ምልክት ነው” በማለት የሠራዊቱን የማይተካ ድርሻ ይገልጻሉ።
ሠራዊታችን ሕይወቱን ሰጥቶ ሀገርን የሚያቆም፣ በችግር ጊዜ ደረቱን ሰጥቶ ሕዝቡን የሚታደግ ሀገራዊ ተቋም ነው።
የመከላከያ ማሻሻያም ሠራዊቱን በዘመናዊ ትጥቅ፣ በቴክኖሎጂ እና በውጊያ ብቃት የላቀ በማድረግ ቀጣናዊ ተፅዕኖ ፈጣሪ የማድረግ ሥራ በተሳካ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጥንካሬ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም የተመሰከረለት ነው። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በአፍሪካ ኅብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ያሳየው እውነተኛ ሀገራዊ ወታደራዊ ሥነ-ምግባር፣ የውጊያ ብቃት እና ለሰላም ያለው ቁርጠኝነት የሌሎች ሀገራትን እና የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን ከፍተኛ አድናቆት እና ምስክርነት አትርፎለታል።
የኢትዮጵያ ሕዝብም ለመከላከያ ሠራዊቱ ያለው ድጋፍ እና ፍቅር አሁንም በከፍተኛ ደረጃ የጸና ነው። ሕዝቡ ሠራዊቱን በቁስ እና በሞራል ድጋፍ ከጎኑ በመቆም ሠራዊቱ የሕዝብ፣ ሕዝብ ደግሞ የሠራዊቱ ደጋፊ መሆናቸውን በተግባር አስመስክሯል።
ኢትዮጵያ ዛሬም በኩራት፣ በነጻነት እና በሉዓላዊነት ፀንታ እንድትቆም ያደረገው የጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን የብረት ክንድ ነው። ይህ ሠራዊት የትናንት ታሪካችን ኩራት፣ የዛሬ ሰላማችን ዋስት እና እና የነገ ተስፋችን መሠረት ሆኖ ይቀጥላል።
#የመደመርመንግሥት
በዮናስ በድሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: