የዓባይ ወንዝን የውሃ ሀብት በፍትሐዊነት በጋራ ከመጠቀም ይልቅ በአረጁ የአንድ ወገን ስምምነቶች ላይ ተመሥርቶ የበላይነትን ለማስቀጠል የሚደረጉ ጥረቶች፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን የቀይ ባሕር መዳረሻ ጥያቄ ለመገደብ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የቀጣናውን የሰላምና የትብብር አጀንዳ እየፈተኑት ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን ለልማት የመገልገልና ብሔራዊ ጥቅሟን የማስጠበቅ ፍላጎቷ ፍትሐዊ በሆነ የሰጥቶ መቀበልና የጋራ ተጠቃሚነት መርህ በሰላማዊ ድርድር መመለስ እንዳለበት ታምናለች።
በግብፅ ኒው አላማይን ከተማ የአስተናጋጇ ግብፅ፣ የሱዳን፣ የኤርትራና የሶማሊያ መሪዎች ያካሄዱት ስብሰባና ያወጡት የጋራ መግለጫ፣ በቀጣናዊ ሰላምና ደህንነት ላይ የኢትዮጵያን ቁልፍ ሚና ያላገናዘበ ነው።
የቀይ ባሕር አስተዳደርና የውሃ ሀብት አጠቃቀም ጉዳይን ጭምር የዳሰሰው መግለጫው የትብብር መንገድን እና ፍትሐዊነትን ከመከተል ይልቅ የጉዳዩን ባለቤትነት “የቀይ ባሕር አዋሳኝ” ላላቸው ሀገራት ብቻ ጠቅልሎ የሰጠ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም።
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ያላት ፍላጎት የሌሎችን ሀገራት ጥቅም መጋፋት ሳይሆን፤ በሰላማዊ ድርድር፣ በሰጥቶ መቀበልና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ መፍትሔ ማግኘት መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጻለች።
የቀይ ባሕር መዳረሻ ለኢትዮጵያ የንግድ፣ የኢኮኖሚ ልማትና የቀጣናዊ ትስስር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ከሀገራዊ ሕልውናና ከረጅም ጊዜ የልማት ፍላጎት ጋር የተያያዘ መሆኑንም ይፋ አድርጋለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት የምስረታ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የዓባይ ውሃንና የቀይ ባሕር ጉዳይን በተናጠል ማየት እንደማይገባ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ የጎረቤት ሀገራትን ጥቅም በሚያከብር መልኩ በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆኗን ገልጸው፣ የሀገራችንን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ወደ ጎን በመተው መፍትሔ ማምጣት እንደማይቻል ተናግረዋል።
“የእናንተን እንካፈል፣ የእኛን ግን አትጠይቁን” የሚል አካሄድ ፍትሐዊነት የጎደለው መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዘላቂ ሰላምና የጋራ ብልፅግና ሊገነባ የሚችለው የሁሉንም ወገኖች ጥቅም በሚያገናዝብ ሚዛናዊ አካሄድ መሆኑን አስረድተዋል።
በዓባይ ወንዝ ዙሪያ ያሉ አለመግባባቶችም በተመሳሳይ መልኩ በፍትሐዊ የጋራ ተጠቃሚነትና በሳይንሳዊ መረጃ ላይ በተመሠረተ ውይይት መፈታት ይገባቸዋል።
ኢትዮጵያ በ1929 እና በ1959 የተደረጉት ስምምነቶች እርሷ ያልተሳተፈችባቸው በመሆናቸው፣ የሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት ጥቅም የሚያስጠብቁ የጋራ የሕግ መሠረት ሊሆኑ እንደማይችሉ በተደጋጋሚ ገልጻለች።
በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ያሉ ልዩነቶች በውይይት ሊፈቱ እንደሚገባም ታምናለች።
በድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብት አጠቃቀም ዙሪያ ፍትሐዊና ምክንያታዊ አጠቃቀምን፣ ጉልህ ጉዳትን ማስወገድንና በቅድሚያ ማሳወቅን የሚመለከቱ መርሆዎችን በጥንቃቄ መተርጎም ያስፈልጋል።
የምክክርና የማሳወቅ ሂደቶች የሌሎችን ሀገራት ስጋት ለመቅረፍና የጋራ መፍትሔ ለማፈላለግ እንጂ፣ የአንድን ሀገር የመልማት መብት ለመገደብ መሣሪያ መሆን የለባቸውም።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በግብፅ ከተካሄደው ስብሰባ በኋላ ባወጣው መግለጫ፣ ሀገራችን በዓባይና በቀይ ባሕር ያላት ብሔራዊ ጥቅም በማንኛውም ቀጣናዊ ውይይት መካተት እንዳለበት አስገንዝቧል።
የኢትዮጵያ ፍላጎቶች በሌሎች ሀገራት መካከል በሚደረጉ ስብሰባዎችና መግለጫዎች ሊወሰኑ እንደማይችሉ የጠቆመው መግለጫው፣ ሀገራችን ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር የምታደርገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል።
የዓባይ ውሃን በፍትሐዊነት መጠቀምና የቀይ ባሕር መዳረሻ ጥያቄን በሰላማዊ ድርድር መፍታት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ብቻ ሳይሆን፣ ለቀጣናው ዘላቂ ሰላም፣ የኢኮኖሚ ትስስርና የጋራ ብልፅግና ጭምር ወሳኝ ነው።
ዘላቂ መፍትሔ የሚመጣው የአንዱን ጥቅም በሌላው ወገን ኪሳራ ላይ ከመመሥረት ይልቅ፣ የሁሉንም ሀገራት መብትና ስጋት በሚያገናዝብ ፍትሐዊ አካሄድ ነው።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: