Search

ኢትዮጵያ በዓለም ባንክ የ22 የአፍሪካ ሀገራት ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ሆና ተመረጠች

እሑድ ጥቅምት 08, 2019 72

ኢትዮጵያ 22 የአፍሪካ ሀገራትን በሚወክለው የዓለም ባንክ ግሩፕ የ‘አፍሪካ ምድብ 1’ የምክትል ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተርነት ቦታ እንድትይዝ ተወሰነ።

የምድቡ አባል ሀገራት የፋይናንስ ሚኒስትሮች እና የብሔራዊ ባንክ ገዢዎች አቶ ሳንዶካን ደበበ ኢትዮጵያንና ምድቡን ወክለው በኃላፊነቱ እንዲሰየሙ የቀረበውን ሹመት ያረጋገጡ ሲሆን፤ ይፋዊ የሥራ ዘመናቸውም ከፈረንጆቹ ሕዳር 1 ቀን 2026 ጀምሮ ይጀምራል።

አቶ ሳንዶካን በቦርዱ የሚወክሉት ምድብ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ አንጎላ እና ሌሎችንም አባል ሀገራት ያካተተ ነው።

ይህ አህጉራዊ ሹመት ኢትዮጵያ በዓለም ባንክ ግሩፕ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛውን የቦርድ አመራር ቦታ እንድትይዝ ያስቻላት ሦስተኛው አጋጣሚ ነው። ቀደም ሲል አቶ ቡልቻ ደመቅሳ (እ.ኤ.አ. ከ1972 እስከ 1974) እንዲሁም ወይዘሮ ሙሉ ከተሰላ (እ.ኤ.አ. ከ2006 እስከ 2008) በዚሁ ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ማገልገላቸው ይታወሳል።

ሹመቱ ለኢትዮጵያም ሆነ ለሰፊው የአፍሪካ ምድብ ወሳኝ ወቅት ላይ የተከናወነ ነው። ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ውስጥ ትልቁ የዓለም ባንክ የልማት ፕሮጀክቶችና የፋይናንስ እንቅስቃሴ ከሚካሄድባቸው አንዷ በመሆኗ፣ በተቋሙ የፋይናንስ አቅርቦትና ፖሊሲዎች ላይ ከፍተኛ ባለድርሻ ያደርጋታል።

በመሆኑም ይህ ኃላፊነት ኢትዮጵያ በዓለም ባንክ የውሳኔ አሰጣጥ ላይ የአፍሪካን ድምፅ ይበልጥ ለማጠናከር ትልቅ ዕድል ይፈጥርላታል።

በመንግሥት አገልግሎትና በልማት ድርጅቶች አመራርነት ሰፊ ልምድ ያላቸው አቶ ሳንዶካን፤ የምድቡን አባል ሀገራት የጋራ ቅድመ-አጀንዳዎች ለማስፈጸም፣ የኢትዮጵያን ተሳትፎ በቦርዱ ውስጥ ለማሳደግ እና ባንኩ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የሚደረጉ ማሻሻያዎችን ለመደገፍ እንደሚሰሩ ይጠበቃል።

በተጨማሪም ከዓለም ባንክ ቦርድ እና ከ22ቱ አባል ሀገራት ጋር በቅንጅት በመስራት በልማት ፋይናንስ፣ በኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ በድህነት ቅነሳ፣ በአየር ንብረት የመቋቋም አቅም ግንባታ እና በግል ዘርፍ እድገት ላይ የጋራ አቋሞችን የሚያስፋፉ ይሆናል።

 

በአጠቃላይ ሹመቱ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የልማት አስተዳደር ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንድታደርግና የአፍሪካን ጥቅም እንድታስከብር የሚያስችል ነው።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: