በአዲስ አበባ ከተማ በ2019 በጀት ዓመት ከ150 በላይ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች እንደሚገነቡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።
ከንቲባዋ ይህን ያሉት በአዲስ መልክ በጥራት ተገንብቶ የተጠናቀቀውን የቄራ አልማዝዬ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳ መርቀው ሥራ ባስጀመሩበት ሥነ-ሥርዓት ላይ ነው።
በአዲስ መልክ የተገነባው የቄራ አልማዝዬ የስፖርት ማዘውተሪያ ለእግር ኳስ ጨዋታ ምቹ የሆነ የሳር ሜዳ፣ የተጫዋቾችና የተቀያሪዎች መቀመጫ፣ የሕፃናት መጫወቻ ሥፍራዎችና የሕክምና ክሊኒክን ጨምሮ በርካታ ዘመናዊ የስፖርት መሠረተ ልማቶችን አሟልቶ የተገነባ ነው።
በምርቃቱ ሥነ-ሥርዓት ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት፤ የቄራ አልማዝዬ ሜዳ ቀደም ሲል ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በርካታ ስመ-ጥር ተጫዋቾችን ያፈራ ታሪካዊ ሥፍራ ነው።
በመሆኑም ሜዳው በጥራትና በደረጃ ተገንብቶ መጠናቀቁ አዲሱን ትውልድ በስፖርትና በሥነ-ምግባር ለማነጽ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ ያግዛል።
አክለውም አሸናፊ እና ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት ለተጀመረው ሀገራዊ ፕሮጀክት፣ ክህሎትና ብቃት ያላቸውን ታዳጊዎች ለማፍራት ማዘውተሪያው ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን ገልጸዋል።
በእግር ኳስና በሌሎች የስፖርት ዘርፎች የሚፈለገውን ሀገራዊ ውጤት ለማስመዝገብ መጠነ-ሰፊ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ማከናወን አስፈላጊ መሆኑን ያመለከቱት ከንቲባዋ፤ በ2019 በጀት ዓመት ብቻ በከተማዋ ከ150 በላይ አዳዲስ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎችን ለመገንባት ዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን አረጋግጠዋል።
#የመደመርመንግሥት
#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በባዬ ሙላት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: