በዘመናዊው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ እና ጂኦፖለቲካዊ ውድድር ውስጥ የሀገራት ዘላቂ ጥንካሬ፣ አካባቢያዊ ተፅዕኖ እና ብሔራዊ ክብር የሚወሰነው በወታደራዊ አቅም ብቻ ሳይሆን በጠንካራ ኢኮኖሚያዊ መዋቅር፣ በምግብ ራስን በመቻል እና በቴክኖሎጂ ዝግጁነት በተደገፈ የዲጂታል ነፃነት ነው።
ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ዘርፎች እያካሄደች ያለችው አጠቃላይ ሽግግርም የመደመር ፍልስፍናን ዋና መሪ እሳቤ በማድረግ ኢኮኖሚያዊ ብልፅግናንና የቴክኖሎጂ የበላይነትን የሀገር ህልውና እና የከፍታ ማረጋገጫ አድርጎ በመቅረጽ ላይ ያተኮረ ነው።
ይህንን የኢኮኖሚ አቅም እንደ ብሔራዊ ኃይል የመጠቀም ስትራቴጂያዊ እቅድ በተግባር ለማሳየት ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለፍጻሜ በቅተዋል።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረትና የሉዓላዊነት ማረጋገጫ የሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ፣ በቢሾፍቱ የሚገነባው ዘመናዊ የአውሮፕላን ማረፊያ፣ የተፈጥሮ ጋዝ እና የማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክቶች የዚሁ ማረጋገጫ ናቸው።
በግብርናው ዘርፍ የተካሄደው መሰረታዊ ለውጥም ከዚህ ቀደም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ይገባ የነበረውን የስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ ሙሉ በሙሉ በመተካት ወደ ውጭ መላክ እንዲጀመር ያስቻለ ሲሆን፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮችና ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች የተደራጀው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ሰፊ የሥራ እድልና የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ ይገኛል።
በተጨማሪም የአዲስ አበባ እና የክልል ከተሞች ኮሪደር ልማት እንዲሁም የወንጪ፣ ጎርጎራ እና ኮይሻ የቱሪዝም መዳረሻዎች ሀገራዊ ገጽታን በቀየረ መልኩ የተገነቡ ሲሆን፣ እነዚህ የልማት ሥራዎች ዘላቂ እንዲሆኑም በአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ኢትዮጵያን በአካባቢ ጥበቃና በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ረገድ አርዓያ አድርጓታል።
በሌላ በኩል የአገልግሎት ዘርፉን ለማሳደግ ሀገራችን ከ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" ወደ "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂካዊ ሽግግር በማድረግ የንግድ፣ የፋይናንስ እና የመንግሥት አገልግሎቶችን አዘምናለች።
የ4G እና 5G ኢንተርኔት፣ የቴሌብር እና መሶብ አገልግሎቶች እንዲሁም የዲጂታል ብሔራዊ መታወቂያ ትግበራ የዜጎችን እንግልት በመቀነስ የእለት ከእለት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን አዘምነዋል።
ሀገራዊ የዲጂታል ነፃነትንና የቴክኖሎጂ አቅምን በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች በኢትዮ ኮደርስ የሰለጠኑ ሲሆን፣ በኢትዮ ስታርት አፕ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና በመከላከያ ሠራዊታችን እየተገነቡ ያሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሀገራችንን የቴክኖሎጂ ምጥቀት አረጋግጠዋል።
እነዚህ አጠቃላይ ጥረቶች ኢትዮጵያ እንደ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ ሰንቃ ዲጂታል ነፃነቷን እና የኢኮኖሚ አቅሟን አጠናክራ ሁለንተናዊ ከፍታዋን እንድታበስር አስችለዋታል።
#የመደመርመንግሥት
#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: