ኢትዮጵያ በልጆቿ ደምና አጥንት የከበረ፣ በጀግንነት የታጀበና በአይበገሬነት የተቀረፀ የሺህ ዓመታት የሉዓላዊነት ታሪክ ባለቤት ናት።
እንደ ብረት በጠነከረ የሕዝቦቿ አንድነትና በብዝሃነት የደመቀው ይህ ታሪካዊ እሴት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ የመጣ የወርቅ አደራ ውርስ ነው።
ከራሷ አልፎ ለአፍሪካውያን የነፃነት ጮራን የፈነጠቀችው እና ለምድር ሁሉ የነፃነት ተምሳሌት ሆና የቆየችው ኢትዮጵያ፣ በየዘመናቱ የውጭ ጠላቶችና የውስጥ ተላላኪዎች የጥፋት ቀስቶችን ቢሰነዝሩባትም ሁልጊዜም እንደ ትንግርት ሆና ትኖራለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት ሀገር ሻጭ እና ሀገር በታኝ ኃይሎች በዲፕሎማሲ ጥምረት እና በውስጥ አለመግባባቶች ሊያዳክሟት ቢሞክሩም ውድቀቷን ሲመኙ ትነሳለች፣ ድክመቷን ሲሹ ትጠነክራለች፣ ተበተነች ሲሉ ተሰብስባ ትገኛለች እንጂ ኢትዮጵያን ግን አልቻሏትም፤ አይችሏትምም።
ይህንን የሀገር ሰላም፣ ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት በፅናት ከማስጠበቅ አንፃር የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በማንኛውም የችግር ማዕበል ውስጥ ያልተበገረ የሀገር ጋሻ ሆኖ ዘልቋል።
ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን ሁሉ ፈተናዎች የሠራዊቱን ተልዕኮ የመፈጸም አቅም እጅግ አጠናክረውታል። በዱር በገደሉ፣ በበረሃው ሀሩር እና በደጋው ውርጭ ሳይበገር የቆመው ይህ ሠራዊት ዛሬ ላይ ሰው አልባ ድሮኖችን፣ ጀቶችንና ታንኮችን ጨምሮ የምድር፣ የአየር፣ የባሕር ኃይል እና የሳይበር ደህንነት ዘርፎችን በዘመናዊ የጦር ሳይንስ አደራጅቷል።
ከዚህም አልፎ የጦር ቴክኖሎጂዎችን ከመግዛት ወደ ማምረት በመሸጋገር የአፍሪካ ኩራት እየሆነ መጥቷል። የሠራዊቱ ድል በጦር ሜዳ ውጊያ ብቻ ሳይሆን የሕዝብ አለኝታና የልማት አጋር በመሆኑ፣ ከዓድዋ ጦርነት ጀምሮ የዘለቀው የሕዝብና የሠራዊት ትስስር የሀገራችን ሰላም፣ አንድነትና ሉዓላዊነት የማፅናት ዋነኛ መሠረት ሆኗል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የዳር ድንበር መከበርን ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ እና የልማት ነፃነትንም እያረጋገጠች ትገኛለች። የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በራሷ አቅም በመገንባት፣ ውስብስብ የጂኦፖለቲካ ደህንነትና የቀይ ባሕር ቀጣናዊ ፍላጎቶችን በጠንካራ ብሔራዊ አንድነት እየተወጣች ነው።
“ከራስ በፊት ለሀገር” በሚል ሀገራዊ ፍቅር የተሞላው የሕዝብና የሠራዊት ጥምረት ለሀገር ክብር የሚከፈለውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን በድሎቹ እያስመሰከረ ይገኛል።
የውስጥ አንድነትን በመጠበቅ፣ በኢኮኖሚ ራስን በመቻልና የሀገራዊ ጥቅምን በዲፕሎማሲው መድረክ በማስከበር የብልፅግና ጉዞዋን እውን እያደረገች የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ የማይበገረውን የጀግንነት ታሪኳን ይዛ የነገውን ትውልድ በኩራትና በነፃነት ለማሻገር በከፍተኛ ተጠንቀቅና በድል ላይ ድልን እየተጎናፀፈች ትቀጥላለች።
#የመደመርመንግሥት
#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: