ሕገ-ወጡ የሕወኃት ቡድን ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የሻዕቢያ ተላላኪ በመሆን ኢትዮጵያ በሕግም ሆነ በተፈጥሮ የነበራትን ታሪካዊ የባሕር በር መብት አሳልፎ በመስጠት ሀገራችንን ባሕር በር አልባ ማድረጉን እና የትግራይን ሕዝብ ከኢትዮጵያዊ ማንነቱ ለመበጠስ ሲሠራ መቆየቱን የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ገለጹ።
ነዋሪዎቹ የቡድኑ የሴራ ፖለቲካ ዕድሜ ማክተሙን ጠቁመው፤ የትግራይ ሕዝብ የጸና ኢትዮጵያዊነቱን በማረጋገጥ ለሀገሩ ታሪካዊ መብት መከበር ከመንግሥት ጎን እንደሚቆም አስታውቀዋል።
"ትግራዋይ ሆኜ ብወለድም ኢትዮጵያዊ ትግራዋይ ነኝ እንጂ ከኢትዮጵያ ውጭ አይደለሁም" ሲሉ የገለጹት አንድ የክልሉ ነዋሪ፤ ሕገ-ወጡ ሕወኃት የትግራይ ክልልን ከኢትዮጵያ የመነጠል ሕልም ቢኖረውም ሕዝቡ ግን በሐሰት ሳይታለል ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር በደም የተሳሰረ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላኛው ነዋሪ በበኩላቸው ሕገ-ወጡ ሕወኃት ትግራይን ከኢትዮጵያ የመነጠል ፍላጎት ቢኖረውም ሕዝቡ ግን የአህጉሪቱን ሰላምና ልማት የሚሻ መሆኑን ገልጸው፣ አሁንም ከመንግሥት ጎን መሆናቸውን በአጽንኦት ተናግረዋል።
የሕወኃት አመጣጥና መሠረት ተሸፍኖ የመጣ የሻዕቢያ አሽከርነት እንደነበር ያነሱት ሌላኛው ነዋሪ፤ ቡድኑ ከሻዕቢያ ጋር በመሆን ቀይ ባሕር የኤርትራ ብቻ እንድትሆን ማድረጉን ጠቁመዋል።
ለትግራይ ሕዝብ ከማንም በላይ ዋና ጠላት ሻዕቢያ መሆኑን ገልጸው፤ የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ እና ሀገሩ ችግር ውስጥ እንድትገባ የማይፈልግ መሆኑን አብራርተዋል።
በተመሳሳይ ሕገ-ወጡ ሕወኃት በታሪካዊ ከሃዲነቱ የኢትዮጵያን የባሕር በር አሳልፎ መስጠቱ በሕዝብ ብዛት ግዙፍ የሆነችውን ሀገር ወደብ አልባ አድርጓታል ሲሉ የተናገሩት ነዋሪዎቹ፤ የቀይ ባሕር ጉዳይ የሁሉም ኢትዮጵያዊ በመሆኑ በስሕተት የሄደው ታሪካዊ መብት ወደ ዋና ባለቤቱ እንዲመለስ እንደሚሹ አስረድተዋል።
ቀይ ባሕር የደማችን እና የሀገራችን አካል በመሆኑ በዚህ ጥያቄ መመለስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተጠቃሚ ይሆናል ሲሉ አመልክተዋል።
በመጨረሻም የክልሉ ነዋሪዎች የሴራ ፖለቲካና የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ዕድሜ ማክተሙን ገልጸው፤ የትግራይ ሕዝብ ማንነቱን አስከብሮና የሻዕቢያን ሴራ ነቅቶ በመረዳት ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር ወደፊት መጓዙን እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል።
ነዋሪዎቹ የባሕር በር ጥያቄው እንዲመለስና ሀገራዊ ፍላጎቱ እንዲሳካ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈልና የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።
#የመደመርመንግሥት
#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: