በዓለም አቀፉ የፋይናንስና የጂኦፖለቲካ ምህዳር ውስጥ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እየተጻፈ ይገኛል። የብሪክስ (BRICS) አባል ሀገራት የማዕከላዊ ባንኮቻቸውን የመጠባበቂያ ወርቅ ክምችት በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ ላይ ናቸው።
ይህም አንድ ገንዘብ የዓለም አቀፍ የበላይነት የመቀነስና የፋይናንስ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ አዲስ አህጉራዊ ትግል መጀመሩን ያመላክታል።
በቅርቡ ይፋ በተደረጉ የፋይናንስ መረጃዎች መሠረት የብሪክስ ሀገራት የወርቅ ክምችት ከስድስት ሺህ ቶን በላይ የደረሰ ሲሆን፣ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ በማዕከላዊ ባንኮች ከተያዘው ሙሉ የወርቅ ክምችት 17.4 በመቶ ድርሻ ይይዛል።
በአውሮፓውያኑ 2019 ከነበረበት 11.2 በመቶ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ እድገት ያሳየው ይህ ክምችት የብሪክስ አባል ሀገራት ከአንድ ዋልታ የፋይናንስ ተጽዕኖ እና ከአንድ የክፍያ ስርዓት እገዳዎች ነፃ የሆነ በራሳቸው ካዝና የሚቀመጥ አስተማማኝ ሀብት ለመገንባት ያላቸውን ጽኑ ቁርጠኝነት ያሳያል።
ይህ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የብሪክስ የፋይናንስ ስትራቴጂ ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ከምታስመዘግበው የወርቅ ምርትና የወጪ ንግድ እድገት ጋር ቀጥተኛ የፖሊሲና የኢኮኖሚ ትስስር አለው።
ሀገራችን ኢትዮጵያ የወርቅ ሀብቷን በጥሬው ከመሸጥ የሞኝ አካሄድ ወጥታ ከፍተኛ ሀገራዊ እሴት ወደሚፈጥርበት ወርቃማ ምዕራፍ ተሸጋግራለች።
በ2018 ዓ.ም ከወርቅ ወጪ ንግድ ብቻ 5.7 ቢሊዮን ዶላር በማስገኘት ታሪካዊ ውጤት አስመዝግባለች።
ይህ ስኬት ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ የቆመች #ትልቅሀገር፣ የሥራ ባህሉን ያደሰ #ትልቅሕዝብ እና ለወደፊቱ የተዘረጋ #ታላቅርዕይ ያላት ሀገር መሆኗን በተግባር ያረጋገጠ፤ የተፈጥሮ ሀብቶቿን በጥሬ ዕቃነት ከመሸጥ ይልቅ እሴት ጨምራ ለዓለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብ የያዘችውን ብሔራዊ ራዕይና የብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ሪፎርም ውጤታማነት የሚያበስር ነው።
ኢትዮጵያ በዓመት ከስድስት መቶ ቶን በላይ ውድ ማዕድናትን የማጣራት አቅም ያለው የመጀመሪያውን ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ እውን ማድረጓ በዘርፉ የታየ ሌላው ታሪካዊ የማድረግ አቅም ማሳያ ነው።
ይህ ማጣሪያ ፋብሪካ የወርቅ ሀብትን በሀገር ውስጥ በማቀነባበር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንድታስገኝ፣ የቴክኖሎጂና የክህሎት ሽግግር እንድታመጣ ከማስቻሉም በላይ፣ ከምስራቅ አፍሪካና ከአህጉሪቱ የማዕድን አቅርቦትን ለመሳብ አዲስ ታሪካዊ ዕድል ፈጥሯል።
ይህ የሀገር ውስጥ የማጣራትና እሴት የመጨመር አቅም፣ የብሪክስ ሀገራት የወርቅ ክምችታቸውን በማሳደግ የዶላር ድርሻን እየቀነሱ በሚገኙበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ የምታመርተውንና የምታጣራውን ወርቅ ለአገራዊ የመጠባበቂያ ሀብትና ለውጭ ንግድ በማዋል የፋይናንስ ተቋቋሚነቷን እንድታጎለብት ያደርጋታል።
በተመሳሳይ መልኩ የወርቅ ማጣሪያ ፋብሪካው መገንባት ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የወርቅ ማጣራትና የወጪ ንግድ ማዕከል እንድትሆን በማድረግ፣ በብሪክስ ማዕቀፍ ውስጥ የሚደረጉ የደቡብ-ደቡብ የኢኮኖሚ ትብብሮችን በከፍተኛ ሁኔታ ያፋጥነዋል።
የብሪክስ ሀገራት የመጠባበቂያ ወርቅ ክምችታቸውን ማሳደጋቸው እና የኢትዮጵያ የወርቅ ምርትና እሴት የመጨመር አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉ፣ የሰርክ የገበያ እንቅስቃሴ ሳይሆን የደቡበ ዓለም ሀገራት ከባህላዊ የምዕራባውያን የፋይናንስ ተጽዕኖ ነፃ የሆነ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያደርጉት የተቀናጀ የጂኦፖለቲካዊ ውሳኔ ውጤት ነው።
ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ያበበውን የወርቅ ሀብት ማልማትና የማጣራት አቅም ከብሪክስ የፋይናንስ ስትራቴጂ ጋር በማቀናጀት፣ የራሷን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ከመጠበቋም ባሻገር በቀጣዮቹ ዓመታት በዓለም አቀፉ የወርቅ ገበያና በብሪክስ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ውስጥ ድምጻቸውንና ሚናቸውን ከፍ የሚያደርጉ አህጉራዊ አጋሮችን አሰልፋ የምትቀጥል ይሆናል።
በሰለሞን ገዳ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: