Search

የአፍሪካ ዋንጫ ወደ ቤቱ እየተመለሰ ነው

ሰኞ ጥቅምት 09, 2019 71

ወርኃ የካቲት 1968 ዓም 10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ተከናወነ። ያ ውድድር ለአፍሪካ ዋንጫ መስራቿ ሀገር የመጨረሻ መስተንግዶዋ ነበር። ያኔ ስምንት ሀገራት ተሳትፈዋል። ሞሮኮ ሻምፒዮን በሆነችበት በዚህ አፍሪካ ዋንጫ በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ስታዲየሞች ነበር ጨዋታዎች የተካሄዱት።

 

ከ51 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጅበት ግዜ አሁን ነው ብላ ጥያቄ አቅርባለች። ሰሞኑን ደግሞ በገለልተኛ ቡድን ዝግጅቷን እያስገመገመች ነው።

 

ከ51 ዓመታት በኋላ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በከፍተኛ እድገት እና ለውጥ ላይ ነው። አዳዲስ ስታዲየሞች ተገንብተዋል፤ የነበሩትም ተሻሽለዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስታር አሊያንስ አባል ነው። ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችም ተገንብተዋል። ከተሞች ተስፋፍተዋል። እናም የብዙ ነገር ቀዳሚ የሆነችው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን የምታስተናግድበት ግዜው አሁን ነው።

 

የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ የሚያስፈልጉ ስታድየሞች

ካፍ የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ቢያንስ 6 ስታዲየሞችን ይጠይቃል። ከነዚህ ውስጥ ሁለቱ ቢያንስ 40 ሺህ ደጋፊዎችን መያዝ የሚችሉ መሆን ይኖርባቸዋል። እነዚህ ስታዲየሞች የመክፈቻና መዝጊያ ጨዋታዎችን ማከናወን የሚያስችሉ ናቸው።

በዚህ ረገድ አደይ አበባ እና ባህር ዳር ስታዲየሞች ከ50 ሺህ በላይ ተመልካች እንዲይዙ ተደርገው እየተሰሩ ናቸው። የአደይ አበባ ስታዲየም ጥራት እና እየተሰራ ያለበት ፍጥነት አስደናቂ ነው። ደረጃው የዓለም ዋንጫ ጨዋታን ማስተናገድ በሚያስችል ልክ ነው። ዘመኑ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂም ታጥቋል። ስታዲየሙ አሁን ላይ ጣሪያ እየተሰራለት ነው። በአጭር ግዜም ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ሌላኛው ባህር ዳር ኢንተርናሽናል ስታዲየም ነው። አሁን ላይ ካታጎሪ 3 ላይ ይገኛል።  ጥራቱ ብዙዎችን ያስገረመ ሜዳ ሲሆን፤ ዓለም አቀፍ ምስክርነትም አለው። 

ቀሪዎቹ አራት ስታዲየሞች ደግሞ የአዲስ አበባው አቃቂ ቃሊቲ ስታድየምን ጨምሮ ጅማ፣ አርባ ምንጭ፣ ሀዋሳ፣ ድሬዳዋ ላይ በቀጣዮቹ ሁለት አመታት መጠናቀቅ ይችላሉ። ከትናንት ስህተት ትምህርት የወሰዱት ስታዲየሞቻችን ዛሬ ላይ የካፍ እና የፊፋን የስታዲየም መስፈርቶችን አሟልተው እየተገነቡ ነው።

 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ጥያቄ ስታቀርብ አንድ ትልቅ ነጥብ የምታስመዘግበው የአፍሪካ ኩራት በሆነው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው። የስታር አሊያንስ አባል የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ያስተሳሰረ ነው። በአፍሪካ ከ40 በላይ በሆኑ ሀገራት 62 መዳረሻዎች አሉት።

የአፍሪካ ዋንጫን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ለማየት ለሚፈልጉ አፍሪካዊያን እንዲሁም በመላው ዓለም ላሉና የአፍሪካ ዋንጫን መታደም ለሚፈልጉ ሁሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቅርባቸው ነው። በሀገር ውስጥም ውድድሮች በሚደረጉባቸው ከተሞችና መጎብኘት ወደሚፈልጉበት ስፍራ ሁሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መዳረሻ አለው።

ሆቴሎችና መስተንግዶ

አሁን ላይ ኢትዮጵያ በሆቴል ዘርፍ በአፍሪካ ተጠቃሽ ነች። ውድድሮችን ለማስተናገድ በታሰበባቸው ከተሞች ሁሉ ባለ 5 ኮከብ ሆቴሎች ይገኛሉ። አንዳንድ የአፍሪካ ዋንጫን ያስተናገዱ ሀገራት በርዕሰ መዲናቸው ካላቸው ሆቴሎች በበለጠ የኢትዮጵያ የክልል ከተሞች ደረጃቸው ከፍ ያሉ ሆቴሎች አሏቸው።

ሆስፒታሎች

 

ካፍ የአፍሪካ ዋንጫን የሚያስተናግድ ሀገር ሲመርጥ ከማይደራደርባቸው መስፈርቶች አንዱ የህክምናው ዘርፍ ነው። ለውድድሩ በተመረጡ ሁሉም ስፍራዎች ደረጃቸው የላቁ ሆስፒታሎች አሉ። በቦታው የሚያስፈልገውን የህክምና መሳሪያዎች እና የሰው ኃይል ለማቅረብም ችግር የለም። 

 

የኢንተርኔት ተደራሽነት

ኢትዮጵያ ከአብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ቀድማ 5G ኔትዎርክን አስጀምራለች። ይህ የኔትዎርክ ዝርጋታ በክልሎችም ጭምር መሆኑ የተለየ ያደርገዋል። አሁንም ኢትዮ ቴሌኮም በከፍተኛ እድገት ላይ በመሆኑ አዳዲስ አሰራሮች ገቢር ማደረጋቸው አይቀርም።

 

ልምድ

ኢትዮጵያ ትላልቅ ሁነቶችን የማስተናገድ ልምድ አላት። ከውድድርም በላይ የሁሉም የአፍሪካ ሀገራት የሚታደሙበትን የመሪዎች ጉባዔን በየዓመቱ ታስተናግዳለች። የአፍሪካ ዋንጫን 3 ግዜ አስተናግዳለች። የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪ የአትሌቲክስ ውድድርንም በከፍተኛ ጥራት ከውናለች። በየጊዜው የሚደረጉ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን የማስተናገድ ልምድም የዳበረ ነው።

እነዚህ ሁሉ የአፍሪካ ዋንጫን የማስተናገዱ እድል ቢሰጥ ለልህቀቱ ማስረጃ ይሆናሉ። ከምንም በላይ እግር ኳስን አብዝቶ የሚወድ ህዝብ አለ፤ በውድድር ግዜ የስታዲየም ወንበሮች ጦማቸውን አያድሩም። የኢትዮጵያዊያን ባህል የሆነው እንግዳ ተቀባይነትም ትልቅ አሴት ነው።

እነዚህ ነገሮች ሁሉ ተደምረው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን እንድታዘጋጅ ዕድል ቢሰጣት የሚያንስባት ነው። የአፍሪካ ዋንጫ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱ አይቀሬ ነው። የመደመር መንግስት 37ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኢትዮጵያ እንዲከናወን እየሰራ ነው።ከሰሞኑም ገለልተኛ ገምጋሚ ቡድን በኢትዮጵያ እየተዘዋወረ ሁኔታዎችን እያጤነ ነው። የአፍሪካ ዋንጫ ወደ ተመሰረተበት ስፍራ፣ ወደ ቤቱ፣ ወደ ኢትዮጵያ እየመጣ ነው።

በሀብታሙ ካሴ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: