መቀመጫውን በዱባይ ያደረገው ታዋቂው አልበዳድ ግሩፕ (Al Baddad Group) በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል።
በአቡዳቢ የኢፌዴሪ ኤምባሲ ተጠባባቂ ጉዳይ ፈጻሚ አቶ ኬኔሳ መኮንን ከግሩፑ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችውን ሰፊ የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ በበርካታ መስኮች የሚገኙ እምቅ የኢንቨስትመንት አቅሞችን እና ምቹ ሁኔታዎችን አስመልክተው ሰፊ ገለጻ አድርገዋል።
የአልበዳድ ግሩፕ ኃላፊዎች በበኩላቸው፣ የቡባንያቸውን አጠቃላይ የኢንዱስትሪ እና ኢንጂነሪንግ ፕሮፋይል ያስተዋወቁ ሲሆን፣ በቀጣይ በኢትዮጵያ በተለይም በማኑፋክቸሪንግ እና በኮንስትራክሽን ዘርፎች በሰፊው ለመሰማራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ከውይይቱ በተጨማሪ የኤምባሲው ቡድን በዱባይ ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ የሚገኘውን የግሩፑን ግዙፍ ፋብሪካዎች የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝቷል፤ በቆይታውም የብረታ ብረት፣ የፒቪሲ (PVC)፣ የፕሪፋብ (Prefab) ቤቶች እና የተለያዩ ተዛማጅ ውጤቶችን የምርት ሂደት ተመልክቷል።
አቶ ኬኔሳ መኮንን ግሩፑ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ያሳየውን ፍላጎት በማድነቅ፣ ይህ ውጥን እንዲሳካ እና ወደ መሬት እንዲወርድ ኤምባሲው አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ ማረጋገጣቸውን በአቡዳቢ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
እ.አ.አ. በ1971 የተመሠረተው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአራት ሺህ በላይ ሠራተኞች ያሉት አልበዳድ ግሩፕ በብረታ ብረት፣ በጊዜያዊ እና ቋሚ ሕንፃዎች፣ በፕሪፋብ እንዲሁም በሞጁላር ኮንስትራክሽን ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ ግዙፍ ኩባንያ ነው።
#የመደመርመንግሥት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: