Search

አዲስ አበባ የአረንጓዴ ሽፋኗን ወደ 25 በመቶ አሳድጋለች

ቅዳሜ ኅዳር 19, 2019 103

በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለው የልማት ሥራ ከኮንክሪት ጫካ ወደ ውብ እና አረንጓዴ ከተማ የሚደረግ ታሪካዊ ሽግግር ነው።

የዘመናዊ ከተማ ስኬት የሚለካው በረጃጅም ሕንጻዎችና በመንገዶች ብቻ ሳይሆን፣ ነዋሪዎች ከተፈጥሮ ጋር ተስማምተው የሚኖሩባቸውን አረንጓዴ ስፍራዎች በማካተት ጭምር ነው።

ለዓመታት የከተማዋ ዕድገት ወደ ኮንክሪት ግንባታ ያደላ ሲሆን፣ የአረንጓዴ ሽፋንም ወደ 2.8 በመቶ አሽቆልቁሎ ነበር።

በዚህም ነዋሪዎች ንጹሕ አየር የሚያገኙባቸውና ከቤተሰብ ጋር የሚዝናኑባቸው ስፍራዎች እጅግ ውስን ነበሩ።

ይህንን ሁኔታ ለመቀየር የተካሄዱት የኮሪደር፣ የወንዝ ዳርቻ፣ የመልሶ ማልማትና የሕዝብ ፓርኮች ፕሮጀክቶች መንገድ ከማስፋት ባለፈ የዛፍ ጥላዎችን፣ የእግረኛ መንገዶችንና አረንጓዴ ስፍራዎችን አካትተዋል። በውጤቱም የከተማዋ የአረንጓዴ ሽፋን ወደ 25 በመቶ ማደግ ችሏል።

ይህ ዕድገት አዲስ አበባ የአየር ንብረት ብክለትን የምትቋቋምና የተመጣጠነ ሙቀት ያላት ከተማ እንድትሆን መሠረት ጥሏል።

እንዲሁም የከተማዋ ነዋሪዎች ንጹሕ አየር ፍለጋ የሚገጥማቸውን ችግር በማቃለል፣ ቀንም ሆነ ማታ በፓርኮች የሚዝናኑበትና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። ጽዱና ደኅንነታቸው የተጠበቁ እነዚህ ስፍራዎች የማኅበራዊ ትስስርና የአብሮነት ማዕከላትም ሆነዋል።

የ25 በመቶ የአረንጓዴ ሽፋን ትልቅ ስኬት ቢሆንም፣ ዓለም አቀፉን የ30 በመቶ ዝቅተኛ መስፈርት ለማሳካት የከተማ አስተዳደሩ እና ነዋሪዎች በትጋት እየሠሩ ነው።

ይህ ጥረት ለዛሬው ትውልድ ምቹ ከተማ ከመፍጠር ባለፈ፣ ሚዛኗን የጠበቀችና ዘላቂ ከተማ ለመጪው ትውልድ የማስረከብ ራዕይ አካል ነው። መረጃው የከንቲባ ጽ/ቤት ነው፡፡

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: