Search

የአፍሪካ ዋንጫ ወደ ቤቱ እየተመለሰ ነው

ሰኞ ጥቅምት 09, 2019 64

ወርሃ የካቲት 1968 ዓ.ም 10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ተከናወነ። ያ ውድድር ለአፍሪካ ዋንጫ መሥራቿ ሀገር የመጨረሻ መስተንግዶዋ ነበር።

ያኔ ስምንት ሀገራት ተሳትፈዋል። ሞሮኮ ሻምፒዮን በሆነችበት በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ፣ በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ስታዲየሞች ነበር ጨዋታዎች የተካሄዱት።

ከ51 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን የምታዘጋጅበት ጊዜ አሁን ነው ብላ ጥያቄ አቅርባለች። ሰሞኑን ደግሞ በገለልተኛ ቡድን ዝግጅቷን እያስገመገመች ትገኛላች።

ከ51 ዓመታት በኋላ፦

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ዕድገት እና ለውጥ ላይ ይገኛል። አዳዲስ ስታዲየሞች ተገንብተዋል፤ የነበሩትም ተሻሽለዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስታር አሊያንስ አባል ነው። ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችም ተገንብተዋል፤ ከተሞች ተስፋፍተዋል። እናም የብዙ ነገር ቀዳሚ የሆነችው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን የምታስተናግድበት ጊዜው አሁን ነው።

የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ የሚያስፈልጉ ስታዲየሞች፦

ካፍ የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ቢያንስ 6 ስታዲየሞችን ይጠይቃል። ከነዚህ ውስጥ ሁለቱ ቢያንስ 40 ሺህ ደጋፊዎችን መያዝ የሚችሉ መሆን ይኖርባቸዋል። እነዚህ ስታዲየሞች የመክፈቻ እና መዝጊያ ጨዋታዎችን ማከናወን የሚያስችሉ ናቸው።

በዚህ ረገድ አደይ አበባ እና ባሕር ዳር ስታዲየሞች ከ50 ሺህ በላይ ተመልካች እንዲይዙ ተደርገው እየተሠሩ ናቸው። የአደይ አበባ ስታዲየም ጥራት እና እየተሠራ ያለበት ፍጥነት አስደናቂ ነው። ደረጃው የዓለም ዋንጫ ጨዋታን ማስተናገድ በሚያስችል ልክ ሲሆን፣ ዘመኑ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂም ታጥቋል። ስታዲየሙ አሁን ላይ ጣሪያ እየተጠመለት የሚገኝ ሲሆን፣ በአጭር ጊዜም ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ሌላኛው የባሕር ዳር ኢንተርናሽናል ስታዲየም ነው። አሁን ላይ ካታጎሪ 3 ላይ ይገኛል። ጥራቱ ብዙዎችን ያስገረመ ሜዳ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ምስክርነትም አለው።

ቀሪዎቹ አራት ስታዲየሞች ደግሞ የአዲስ አበባውን አቃቂ ቃሊቲ ስታዲየምን ጨምሮ ጅማ፣ አርባ ምንጭ፣ ሐዋሳ እና ድሬዳዋ ላይ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት መጠናቀቅ ይችላሉ። ከትናንት ስህተት ትምህርት የወሰዱት ስታዲየሞቻችን ዛሬ ላይ የካፍ እና የፊፋን የስታዲየም መስፈርቶችን አሟልተው እየተገነቡ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ፦

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ጥያቄ ስታቀርብ አንድ ትልቅ ነጥብ የምታስመዘግበው የአፍሪካ ኩራት በሆነው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው። የስታር አሊያንስ አባል የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ያስተሳሰረ ነው። በአፍሪካ ከ40 በላይ በሆኑ ሀገራት 62 መዳረሻዎች አሉት።

የአፍሪካ ዋንጫን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ለማየት ለሚፈልጉ አፍሪካውያን እንዲሁም በመላው ዓለም ላሉ እና የአፍሪካ ዋንጫን መታደም ለሚፈልጉ ሁሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቅርባቸው ነው። በሀገር ውስጥም ውድድሮች በሚደረጉባቸው ከተሞች እና መጎብኘት ወደሚፈልጉበት ስፍራ ሁሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መዳረሻ አለው።

ሆቴሎች እና መስተንግዶ፦

አሁን ላይ ኢትዮጵያ በሆቴል ዘርፍ በአፍሪካ ተጠቃሽ ነች። ውድድሮችን ለማስተናገድ በታሰበባቸው ከተሞች ሁሉ ባለ 5 ኮከብ ሆቴሎች ይገኛሉ። አንዳንድ የአፍሪካ ዋንጫን ያስተናገዱ ሀገራት በርዕሰ መዲናቸው ካላቸው ሆቴሎች በበለጠ፣ የኢትዮጵያ የክልል ከተሞች ደረጃቸው ከፍ ያሉ ሆቴሎች አሏቸው።

ሆስፒታሎች፦

ካፍ የአፍሪካ ዋንጫን የሚያስተናግድ ሀገር ሲመርጥ ከማይደራደርባቸው መስፈርቶች አንዱ የሕክምናው ዘርፍ ነው። ለውድድሩ በተመረጡ ሁሉም ስፍራዎች ደረጃቸው የላቁ ሆስፒታሎች አሉ። በቦታው የሚያስፈልገውን የሕክምና መሣሪያዎች እና የሰው ኃይል ለማቅረብም ችግር የለም።

የኢንተርኔት ተደራሽነት፦

ኢትዮጵያ ከአብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ቀድማ 5G ኔትወርክን አስጀምራለች። ይህ የኔትወርክ ዝርጋታ በክልሎችም ጭምር መሆኑ የተለየ ያደርገዋል። አሁንም ኢትዮ ቴሌኮም በከፍተኛ ዕድገት ላይ በመሆኑ አዳዲስ አሠራሮችን ገቢር ማድረጉ አይቀሬ ነው።

ልምድ፦

ኢትዮጵያ ትላልቅ ሁነቶችን የማስተናገድ ልምድ አላት። ከውድድርም በላይ የሁሉም የአፍሪካ ሀገራት የሚታደሙበትን የመሪዎች ጉባኤ በየዓመቱ ታስተናግዳለች። የአፍሪካ ዋንጫን 3 ጊዜ አስተናግዳለች። የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪ የአትሌቲክስ ውድድርንም በከፍተኛ ጥራት ከውናለች። በየጊዜው የሚደረጉ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን የማስተናገድ ልምድም የዳበረ ነው።

እነዚህ ሁሉ የአፍሪካ ዋንጫን የማስተናገድ ዕድል ቢሰጥ ለልሕቀቱ ማስረጃ ይሆናሉ። ከምንም በላይ እግር ኳስን አብዝቶ የሚወድ ሕዝብ አለ፤ በውድድር ጊዜ የስታዲየም ወንበሮች ጦማቸውን አያድሩም። የኢትዮጵያውያን ባህል የሆነው እንግዳ ተቀባይነትም ትልቅ ዕሴት ነው።

እነዚህ ነገሮች ሁሉ ተደምረው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን እንድታዘጋጅ ዕድል ቢሰጣት የሚያንስባት ነው። የአፍሪካ ዋንጫ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱ አይቀሬ ነው።

የመደመር መንግሥት 37ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኢትዮጵያ እንዲከናወን እየሠራ ነው። ከሰሞኑም ገለልተኛ ገምጋሚ ቡድን በኢትዮጵያ እየተዘዋወረ ሁኔታዎችን እያጤነ ነው።

የአፍሪካ ዋንጫ ወደ ተመሠረተበት ስፍራ፣ ወደ ቤቱ፣ ወደ ኢትዮጵያ እየመጣ ነው።

በሀብታሙ ካሴ

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: