Search

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በሰላማዊ ድርድር እና በ'ሰጥቶ መቀበል' መርሕ ሊፈታ የሚችል ፍትሐዊ ጥያቄ ነው፡- የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር

ሰኞ ጥቅምት 09, 2019 56

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ በሰጥቶ መቀበል መርሕ ሊፈታ የሚችል ፍትሐዊ ጥያቄ መሆኑን በቤልፋስት የኩዊንስ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር የሆኑት ብዙነህ ጌታቸው (ዶ/ር) ተናገሩ።

የሕዝብ ቁጥሯ ከ130 ሚሊዮን በላይ ለሆነው ኢትዮጵያ፣ ቀጥተኛ እና አስተማማኝ የባሕር በር ማግኘት ሕጋዊ መብቷ ብቻ ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል።

መምህሩ ከሲጂቲኤን ‘ቶክ አፍሪካ’ ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት የሚመሩ ስትራቴጂያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ታሪካዊ ምክንያቶችን አቅርበዋል።

በአንድ የወደብ ኮሪደር ላይ ብቻ ጥገኛ መሆን በሕዝብ ብዛት በአፍሪካ ሁለተኛ ለሆነችው ኢትዮጵያ ከፍተኛ ስትራቴጂያዊ ስጋት እንደሆነም ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የገቢ እና ወጪ ንግዷን 95 በመቶ ገደማ የምታከናውነው በጅቡቲ ነጠላ ኮሪደር በኩል ነው። ዶክተር ብዙነህ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር እጅግ በጣም ቅርብ በሆነ መልኩ በጂኦግራፊያዊ ሁኔታ ተቀምጣ ሳለ፣ ሙሉ በሙሉ የባሕር በር አልባ ሆና መቅረቷ በጂኦፖለቲካው መስክ ልዩ ያደርጋታል።

ይህንን ስጋት ለመቅረፍ የኢትዮጵያ መንግሥት በኃይል ወይም በወረራ ሳይሆን ሁለቱንም ወገኖች በጋራ ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ በሰጥቶ መቀበል መርሕ በንግድ ስምምነቶች በኩል የረጅም ጊዜ የወደብ መሠረተ ልማቶችን ማረጋገጥ፤ ወይም ለወደብቸ እና ለባሕር በር አማራጭ እንደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢትዮ ቴሌኮም ያሉ ታላላቅ የሀገር ውስጥ ተቋማት ድርሻን ለጎረቤት ሀገራት በማቅረብ የዲፕሎማሲ ማዕቀፍ መንገድ ስታቀርብ ቆይታለች።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ እና የጎረቤት ሀገራት ሉዓላዊነት የሚቃረኑ አለመሆናቸውን እና የጎረቤት ሀገራት በጎ ፈቃድ ካላቸው በሰላማዊ መንገድ በውይይት ሊፈታ እንደሚችል አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያን የማሪታይም ታሪካዊ አጋጣሚዎችን እና የሕዝብ ብሔራዊ ስሜቶችን ሲያብራሩ፣ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከመገንጠሏ በፊት ሀገራችን በአሰብ እና በምፅዋ ወደቦች በኩል ሉዓላዊ የባሕር በር እንደነበራት አስታውሰዋል።

የወደብ አገልግሎቱ እ.አ.አ በ1998-2000 በነበረው የድንበር ጦርነት ምክንያት ድንገት በመቋረጡ፣ አዲስ አበባ ሙሉ በሙሉ ንግዷን ወደ ጅቡቲ ለማዞር ስለመገደዷም አንሥተዋል።

እ.አ.አ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የነበረው የሽግግር መንግሥት የኢትዮጵያን የባሕር በር በዘላቂነት አሳልፎ ለመስጠት እና ኢትዮጵያን በጂኦፖለቲካ ደረጃ ጎጂ ሁኔታ ውስጥ ለመክተት ሕጋዊ እና ታሪካዊ ውክልና አልነበረውም ብለዋል።

የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች እየሰጠ ያለውን የውጭ መሣሪያ፣ የሎጂስቲክስ እና የመጠለያ ድጋፍንም ኮንነዋል።

ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ያላትን ሀገር በዘላቂነት ከባሕር በር ለማግለል የሚደረግ ጥረት ፍጹም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ነው ያሰመሩበት።

በምሥራቅ አፍሪካ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የውክልና አፍራሽ ሥራዎችን በአስቸኳይ ማቆም፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማክበር እንዲሁም በቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትሥሥር እና በባሕር በር ጉዳይ ላይ መዋቅራዊ እና ሰላማዊ ውይይቶችን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጥሪ አቅርበዋል።

#የመደመርመንግሥት

#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በላሉ ኢታላ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: