ኢትዮጵያ የታሪክ ፈተናዎችን በጽናት አልፋ፣ የሉዓላዊነቷንና የነጻነቷን ሰንደቅ ዓላማ በከፍተኛ ክብር እና ግርማ አስከብራ ያኖረችው በውድ ልጆቿ ወደር የሌለው መስዋዕትነት ነው።
በዚህ የታሪክና የክብር ማዕከል ደግሞ የሀገር መከታ፣ የሕልውናችን አስተማማኝ ዋስትና እና የመኖራችን ሕያው ምስክር የሆነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ግንባር ቀደም ቦታውን ይይዛል።
ሠራዊታችን ለአንድ ሀገር ከሚከፈል ማንኛውም ዋጋ በላይ ደሙን አፍስሶ እና ሕይወቱን ሰውቶ ሀገርን የጸናች የሚያደርግ እውነተኛ የሀገር ፍቅር መገለጫ ነው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባል መሆን ተራ የሥራ ዕድል ወይም የሙያ ምርጫ ሳይሆን፣ ለሀገር ክብር እና ለሕዝብ ደህንነት ሕይወትን አሳልፎ ለመስጠት የተገባ የከበረ ቃል ኪዳን ነው።
በበረሃው ቃጠሎ፣ በደጋው ቅዝቃዜ፣ በዝናቡ እና በቁሩ ውስጥ ሳይበገር ሌሊት እና ቀን በንቃት የሚጠብቀን ይህ ሠራዊት፣ እኛ በሰላም ወጥተን እንድንገባ የራሱን ሰላምና እረፍት አሳልፎ የሰጠ አስተማማኝ ጋሻችን ነው።
የሚከፍለው ዋጋ በገንዘብ ወይም በቁሳቁስ የሚለካ ሳይሆን፣ የትውልድን ህልውና የሚያስቀጥል ውድ ሕይወቱን ነው። የሠራዊታችን ተልዕኮ የሀገርን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት በመጠበቅ ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን፣ በሀገር ግንባታ እና በልማት እቅዶች ውስጥም ቢሆን ግንባር ቀደም ተሳታፊና ሕያው አጋር ነው።
በትልልቅ የሀገር ሀብትና መሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ በተፈጥሮ አደጋዎች ጊዜ ደራሽ በመሆን፣ እንዲሁም የሕዝብን ችግር በመካፈል ረገድ የሚያሳየው ትጋት የልማታችንም ምሰሶ መሆኑን አስመስክሯል።
በጦር ሜዳ የጀግንነት ጋሻ፣ በልማት ሜዳ ደግሞ የጽናትና የትጋት ሞተር ሆኖ የሚያገለግል ድንቅ ጥንካሬ ያለው ሠራዊት ነው። በዓለም ላይ በርካታ የዘመነ ትጥቅና ቴክኖሎጂ ያላቸው ሠራዊቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ያለው ዓይነት የታመነ፣ ፅኑ እና ለሀገር በፍቅር የሚቃጠል ልብ ያለው ሠራዊት ማግኘት እጅግ ፈታኝ ነው።
የመከላከያ ሠራዊታችን ግርማ ሞገስ ያለው ጥንካሬ ከትጥቅ በላይ ከውስጥ ከሚመነጭ የጀግንነት እና የሀገር ፍቅር መንፈስ የሚወለድ ነው። በፈተናዎች ውስጥ ሲያልፍ የማይበገረው፣ በጥቅም የማይደለለው እና ሀገሩን ከምንም ነገር በላይ አስበልጦ የሚወደው ይህ ወርቃማ ልቡ፣ የኢትዮጵያን ጠላቶች የሚያስከዳና ወዳጆቿን የሚያኮራ የኃይሉ ምስጢር ነው።
ዛሬ ያገኘነው ሰላም፣ ወጥተን የመግበታችን እድል እና የሀገራችን ቀጣይነት በሙሉ የመከላከያ ሠራዊታችን አባላት በየግንባሩ በሚከፍሉት የከበረ ዋጋ እና በልማት መስክ በሚያፈሱት ላብ የተገነባ በመሆኑ፣ መላው ኢትዮጵያውያን ዛሬም እንደ ትላንቱ ከሀገር መከታው ሠራዊታቸው ጎን በፍቅር፣ በደስታና በኩራት በመቆም ያልተገደበ አጋርነታቸውን እያሳዩ ይገኛሉ።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: