Search

ኢትዮጵያ በሰው ሠራሽ አስተውሎትና በዲጂታል ክህሎት ልማት የታገዘ የሰው ሀብት ግንባታ ላይ በትኩረት እየሠራች ትገኛለች፦ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

ሰኞ ጥቅምት 09, 2019 54

ኢትዮጵያ በሰው ሀብት ልማት፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና በዲጂታል ክህሎት ዘርፎች ሰፊና ስትራቴጂካዊ ተግባራትን እያከናወነች መሆኗን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ  ኢዮብ ተካልኝ  (ዶ/ር) ገለጹ።

ለክህሎት ልማት የግል ካፒታልን በማሰባሰብ ላይ በሚያተኩረው የሰው ሀብት ልማት ሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ የተገኙት ኢዮብ ተካልኝ  (ዶ/ር)  ለዘርፉ መሠረት ለመጣል በርካታ ሀገራዊ እርምጃዎችን መውሰዱን አብራርተዋል።

በዚህም ሀገራዊ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ፖሊሲ፣ የኢትዮጵያ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት፣ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030፣ የአምስት ሚሊዮን ኮደሮች ፕሮግራም እና የመደመር ሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በርካታ አቅም የሚገነቡ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰው ሠራሽ አስተውሎት አሰልጣኝና የትምህርት አጋዥ መሣሪያዎችን በሙከራ ደረጃ በመተግበር ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበርም ለቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት የሚያገለግል በሰው ሠራሽ አስተውሎት የታገዘና የሥርዓተ-ፆታ ተገቢነትን ያካተተ የክህሎትና የሥራ ዕድል ማገናኛ መድረክ ለማቋቋም እየተሠራ መሆኑን የጠቀሱት ገዥው፣ መድረኩ ለስደተኛ ወጣቶችና በአስተናጋጅ ማኅበረሰቦች ውስጥ ለሚገኙ ወጣቶችም የሥራ እድል ተደራሽነትን ለማሳደግ እንደሚረዳ አመልክተዋል።

በክህሎት ልማት ረገድ መንግሥት አሠሪዎችና የሥልጠና ተቋማት የጋራ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበው፣ የሥልጠና ስኬትም ሰልጣኞች ለሥራ ገበያው ተፈላጊ የሆኑ ክህሎቶችን ማግኘታቸውና የሥራ ዕድላቸው መሻሻሉ ላይ ተመሥርቶ መመዘን እንዳለበት ጠቁመዋል።

የግል ካፒታልን ወደ ክህሎት ልማት ለማሳተፍ ግልጽ የሆኑ የሕዝብ ቅድሚያ ተግባራት የጥራት ደረጃዎችና ፍትሐዊ የተደራሽነት ሥርዓት መኖር እንደሚገባ አስረድተዋል።

ይህ የቴክኖሎጂና የክህሎት እመርታ ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ የተገነባች #ትልቅሀገር፣ የነገውን ዘመን የሚቃኝ #ትልቅሕዝብ እና ለወደፊቱ የተዘረጋ #ታላቅርዕይ ያላት ሀገር መሆኗን በዓለም አቀፍ መድረክ በተግባር ያረጋገጠ ነው።

በዓለም ባንክ ቡድን የሰው ሀብት ልማት ፕሮጀክት (Human Capital Project) በተዘጋጀው በዚህ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ከምሥረታው ጀምሮ ንቁ ተሳትፎ እያደረገች ትገኛለች።

በኢንቲሃድ አብራር

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: