በአሁኑ የቴክኖሎጂ ዘመን የዲጂታል አገልግሎቶች መስፋፋት የዜጎችን እንግልት በመቀነስ ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። በአንፃሩ ዲጂታል አገልግሎቶቹ ተደራሽ በሆኑ ቁጥር፣ ከዘመኑ የሳይበር ጥቃት ስጋት የተጠበቁ መሆናቸውን ማረጋገጥ የሕልውና ጉዳይ ነው። የኅብረተሰቡን የመረጃ እና የዲጂታል ደህንነት ማረጋገጥ የዲጂታል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቀዳሚ የቤት ሥራ ሆኗል።
ይህን ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት መሠረት በማድረግ፣ የፌዴራል መሶብ አገልግሎት "ንቁ ዜጋ፣ ደህንነቷ ለተጠበቀ ሀገር" በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን 7ኛውን ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር በማስመልከት ለአመራሩና ለሠራተኞቹ የአንድ ሳምንት የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብር አዘጋጅቷል።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የፌዴራል መሶብ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮናስ አለማየሁ፣ ተቋሙ በሀገር አቀፍ ደረጃ በከፈታቸው 113 ቅርንጫፎቹ አማካይነት የ28 ተቋማትን ከ243 በላይ አገልግሎቶች አቀናጅቶ እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
እነዚህን አገልግሎቶች ከየትኛውም ዓይነት የሳይበር ጥቃት ስጋት ነጻ ማድረግ እና ሁሌም ዝግጁ መሆን የተቋሙ ዋነኛ ግብ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህም አርዓያ የሚሆን ተቋማዊ የቴክኖሎጂ ፖሊሲ አውጥቶ ወደ ሥራ መግባቱን አብራርተዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ተወካይ ጥላሁን እጅጉ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ መሶብ የኅብረተሰቡን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚፈታ ዲጂታል አገልግሎት ሰጪ ተቋም በመሆኑ፤ የተቋሙን የሳይበር ደህንነት ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
እንደ መሶብ ባሉ ተቋማት የሳይበር ደህንነት ጉዳይን በስትራቴጂክ ደረጃ መምራት ቁልፍ ሥራ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የፌዴራል መሶብ አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አንተነህ ማሞ በመድረኩ ማጠቃለያ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የሳይበር ደህንነት ሥራ ችግር ከተከሰተ በኋላ ምላሽ መስጠትን ብቻ ሳይሆን አስቀድሞ መከላከልን የሚጠይቅ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም ሁሉም የመሶብ አገልግሎት አመራርና ሠራተኞች በየዕለቱ በሚሰጡት አገልግሎት የሳይበር ደህንነትን የማረጋገጥ ሥራን ከዋና ሥራቸው እኩል ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
7ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር “ንቁ ዜጋ፣ ደህንነቷ ለተጠበቀ ሀገር” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ሲሆን፤ ይህን መሠረት በማድረግ የተለያዩ ተቋማትም እንደ ሥራ ባሕሪያቸው ንቅናቄውን በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: