Search

በ40 A+ የታጀበው የፅዮን ብዙነህ አስገራሚ የስኬት ጉዞና የሜዳሊያዎቹ ምስጢር

ሓሙስ መጋቢት 17, 2018 11

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ 30ኛው ዙር የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የብዙዎችን ቀልብ የሳበና የመነጋገሪያ አጀንዳ የሆነ አንድ ድንቅ ታሪክ ተመዝግቧል።
የጤናና ሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ ካስመረቃቸው 616 ተማሪዎች መካከል በሥነ አዕምሮ (ሳይካትሪ) ትምህርት ክፍል ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው ወጣት ፅዮን ብዙነህ የዕለቱ ደማቅ ኮከብ ሆናች።
ፅዮን በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ በወሰደቻቸው 43 የትምህርት አይነቶች ውስጥ በ40ዎቹ "A+" እና "A" በማምጣት በአካዳሚው ዓለም አስደናቂ የሚባል ብቃቷን አስመስክራለች።
ይህ ተከታታይና ድንቅ ውጤቷም የከፍተኛ ማዕረግ የወርቅ ሜዳሊያና የሁለት ዋንጫዎች ባለቤት እንድትሆን አስችሏታል።
ለዚህ ስኬቷ መሠረቱ መነሻን አለመርሳት፣ ዓላማን መሰነቅና ተግቶ መስራት መሆኑን የምትገልጸው ፅዮን፤ የዩኒቨርሲቲ ሕይወት ፈተናዎች ቢበዙበትም በጽናት ለሚጓዝ ሰው ስኬት አይቀሬ መሆኑን በተግባር አሳይታለች።
በተለይም ለማህበራዊ ጫናዎች ሳይሸነፉ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል በማረጋገጥ ለሴት ተማሪዎች ትልቅ አርአያ ሆና ቀርባለች።
ለስኬቷ የሐረር ማህበረሰብ ፍቅር፣ የመምህራኖቿ የቅርብ ክትትልና የቤተሰቦቿ የማይለወጥ ድጋፍ ትልቅ አቅም እንደሆናት የምታወሳው ተመራቂዋ፤ ይህ ውጤት ለእሷ ገና መነሻ መሆኑን ትናገራለች።
"ከዚህ በላይ በመማርና በመስራት፣ ተቸግረው ያሳደጉኝን ቤተሰቦቼንና ማህበረሰቤን በቅንነት ለማገልገል እሰራለሁ" ስትልም የወደፊት ራዕይዋን ገልጻለች።
ፅዮን ብዙነህ በለጋ ዕድሜዋ ያስመዘገበችው ይህ ታሪካዊ ውጤት፣ ታታሪነትና ጽናት ካለ የማይታለፍ ፈተናም ሆነ የማይደረስበት የሥኬት ማማ እንደሌለ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው።
በቢታኒያ ሲሳይ