Search

“ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ከውጭ የምናስገባውን የሴራሚክ ምርት እናስቀራለን” - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ቅዳሜ ግንቦት 15, 2018 123

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምሥራቅ ሸዋ ዞን፣ ሞጆ ከተማ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ ተገንብቶ የተጠናቀቀውን የግራንዴር ሴራሚክ ፋብሪካ መርቀው ከፍተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢትዮጵያ ለግንባታ ማጠናቀቂያ የሚሆኑ ሴራሚክ፣ ማርብል እና ግራናይት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ዛሬ ከተመረቀው የሴራሚክ ፋብሪካ በተጨማሪ በቅርብ ጊዜ ደብረ ብርሃን አካባቢ ሌላ ከፍተኛ አቅም ያለው የሴራሚክ ፋብሪካ እንደሚመረቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብስረዋል።

ዛሬ የተመረቀውን ጨምሮ ሌሎች ፋብሪካዎች ወደ ሥራ ሲገቡ ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮም የሴራሚክ ምርቶችን ከውጭ ማስገባት እናስቀራለን ነው ያሉት።

በተጨማሪም የሀገር ውስጥ አቅምን ሙሉ ለሙሉ ለማሳደግ በሲሚንቶ እና ብረት ማምረት ዘርፍ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች በፍጥነት እየተሠሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ በሲሚንቶ ረገድ የነበረውን ፍላጎት ለማሟላት ታላቅ አስተዋፅኦ ማደረጉን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ማስፋፊያውን በቅርቡ የሚያጠናቅቀው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ፍላጎታችንን በአስተማማኝ ሁኔታ እንደሚያሟላ ገልጸዋል።

በለሚ ታደሰ