ሀገራዊ ምክክር የፖለቲካ ልሂቃን መድረክ ብቻ ሳይሆን የጠቅላላው ኅብረተሰብ ድምፅ የሚሰማበት ታሪካዊ ሂደት ነው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ያከናወናቸውን ተግባራት ስታቲስቲካዊ መረጃዎች ስንመረምር፣ ተቋሙ በመሬት ላይ ያሉ ፈተናዎችን እየተጋፈጠ ምን ያህል ሰፊ ርቀት መጓዝ እንደቻለ ቁጥሮቹ በራሳቸው ጉልህ ምስክርነት ይሰጣሉ።
የአንድ ሀገራዊ ምክክር ስኬት በዋናነት የሚለካው ባረጋገጠው የተደራሽነት መጠን እና ሽፋን ነው።
ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ ከሁሉም የማኅበረሰብ ከፍል የተወከሉ 400 ተሳታፊዎችን ያካተተ መድረክ በማዘጋጀት ነው ሥራውን የጀመረው። በአሁኑ ወቅት የሀገራችንን 93 በመቶ መልክዓ ምድራዊ ወሰን መሸፈን ችሏል።
ከ11 ክልሎች እና ከ2 የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ1 ሺህ 234 በላይ ወረዳዎች ተወካዮቻቸውን በመለየት ለአጠቃላይ ምክክሩ የሚሆኑ የአጀንዳ ሐሳቦችን ለኮሚሽኑ አስረክበዋል።
በእስካሁኑ ሂደት በአጠቃላይ በሀገራችን በተካሄዱት የተለያዩ መድረኮች ከ200 ሺህ በላይ ዜጎች ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆነ ተሳትፎ ማድረግ ችለዋል። ከእነዚህ ውስጥ 126 ሺህ 22 በወረዳ ደረጃ የተመረጡ ቀጥተኛ ተወካዮች ናቸው።
ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተወከሉ ከ1 ሺህ 746 በላይ የጥቃቅን ቡድኖች የምክክር አጀንዳዎች በዝርዝር ተሰንደው ተይዘዋል።
እነዚህ አስደናቂ ቁጥሮች የምክክሩን ሂደት እውነተኛ የሕዝብ ድምፅ ማስተናገጃ አድርገውታል።
ኮሚሽኑ ምክክሩን አካታች ለማድረግ 1 ሺህ 300 ወረዳዎችን፣ 13 ሺህ ቀበሌዎችን እና ከ91 ሺህ በላይ ጎጦችን ያገናዘበ ዝርዝር መዋቅራዊ ስልተ-ቀመር ነድፎ ተግባራዊ አድርጓል።
የኮሚሽኑ አሳታፊነት በማኅበረሰብ ክፍሎች ስብጥር እና በባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ላይም በጉልህ ይንጸባረቃል።
በሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ላይ የሴቶች ተሳትፎ ከ45 በመቶ በላይ እንዲሆን በልዩ ትኩረት ተሠርቷል።
በፌደራል ደረጃ 900 የሚጠጉ የባለድርሻ አካላት ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 220 የሚሆኑት ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ናቸው።
በሌላ በኩል ደግሞ ከ51 የመንግሥት እና ከ5 የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ 1 ሺህ 200 የዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ ኃላፊዎች እና የሥራ መሪዎች በሂደቱ ተሳትፈዋል።
በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት እንዲሁም በዓረብ ኤምሬቶች እና በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ የዳያስፖራ አባላትን ማካተት ተችሏል። በሰሜን አሜሪካም ኮሚሽኑ በአካል በመገኘት የተሳታፊዎችን የአጀንዳ ሀሳብ ተረክቧል።
ከሕዝብ ጋር ያለውን የመረጃ ልውውጥ ለማሳለጥ ደግሞ የ8112 ነፃ የአጭር ስልክ መስመር፣ መደበኛ ስልኮች፣ የፖስታ ሳጥን ቁጥር 32623 እና የኢሜል አድራሻ ለአገልግሎት አቅርቧል።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ም/ቤት፣ የእድሮች ጥምረት፣ የመምህራን ማኅበር እና የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌደሬሽንን ያካተተ የጋራ አስተባባሪ ቡድን መቋቋሙም ተቋማዊ ቅንጅቱን አጠናክሮታል።
እነዚህ ሁሉ ስታቲስቲካዊ መረጃዎች እና ቁጥሮች የሚያረጋግጡት አንድ ትልቅ እውነት የኮሚሽኑን አካታችነት ነው።
በሂደቱም በጂኦግራፊያዊ እውነት ላይ የተመሠረተ እና አስተማማኝ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያስችል ጠንካራ መሠረት ጥሏል።
ኮሚሽኑ እነዚህን ተግባራት አከናውኖ የመጨረሻ ሀገራዊ ምክክር ዋዜማ ላይ ደርሷል። ቀሪው የምክክሩን ውጤት ሥራ ላይ ማዋል ሲሆን፣ እሱ ደግሞ የአጠቃላይ ኅብረተሰቡን እና የልሂቃንን ቀናነት ብቻ ይፈልጋል።
በለሚ ታደሰ
#Ethiopian #NationalDialogue #InclusiveDialogue #NationalConsensus #EBC