በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታየውን የንግድ መስተጓጎል እና የጂኦ-ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ለመቋቋም የብሪክስ (BRICS) የትብብር ማዕቀፍ ለደቡብ-ደቡብ ሀገራት ግንኙነት ዋልታ እየሆነ መምጣቱን የዘርፉ ምሁራን እና የንግድ መሪዎች ገለጹ።
በቤጂንግ በተካሄደው የብሪክስ የንግድ እና ኢኮኖሚ ፎረም ላይ የቀረቡ ወቅታዊ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ስብስቡ በአሁኑ ወቅት የዓለምን የኢኮኖሚ ሚዛን በመቀየር ረገድ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት የብሪክስ ሀገራት በዓለም አቀፍ ጠቅላላ ምርት (GDP) ላይ ያላቸው ድርሻ 30 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ የንግድ ልውውጥ ደግሞ አንድ አምስተኛውን ድርሻ ይዘዋል። ከሁሉ በላይ ትኩረት የሳበው ግን ስብስቡ ለዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከ50 በመቶ በላይ መድረሱ ነው።
በፎረሙ ላይ ንግግር ያደረጉት የቻይና ዓለም አቀፍ የንግድ ማሳደጊያ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ ሊ ቺንግሹዋንግ፣ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታው በግርግር እና ባልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ቢገኝም፣ የብሪክስ ሀገራት ግን የዓለምን ኢኮኖሚ በማረጋጋት እና ዓለም አቀፍ የገበያ መዳረሻዎችን በማስፋፋት ረገድ ቁልፍ ኃይል መሆናቸውን አስረድተዋል።
"የብሪክስ ትብብር ለደቡብ-ደቡብ ሀገራት ልማት" በሚል መሪ ቃል በተካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ፣ አባል ሀገራት በንግድ ልውውጥ ወቅት የሚያጋጥሟቸውን የቴክኒክ እና የጥራት ደረጃ ልዩነቶች በማቀናጀት ምርት እና አገልግሎት በቀላሉ እንዲሸጋገር የሚያስችል "የብሪክስ የንግድ ልማት እና የደረጃዎች ትብብር መመሪያ" ይፋ ሆኗል።
ይህ ሰነድ በአባል ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ፍሰት ከማቀላጠፉም በላይ የአቅርቦት ሰንሰለት ደህንነትን ለማረጋገጥ ትልቅ እመርታ ተደርጎ ተወስዷል።
ይህ ተለዋዋጭ ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ሂደት ለኢትዮጵያም ሰፊ የዕድገት አድማስ ይዞ መጥቷል። ኢትዮጵያ የስብስቡ አባል መሆኗን ተከትሎ፣ መሰል የንግድ መመሪያዎች መውጣታቸው ለሀገር ውስጥ ላኪዎች አዲስ የገበያ በር ይከፍታል።
ይህም እንደ ቻይና፣ ህንድ እና ብራዚል ወዳሉ ሰፊ ገበያዎች ምርቶችን ለመላክ የሚያስፈልጉ የጥራት ደረጃዎችን አስቀድሞ ለማወቅና ለማሟላት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። በተጨማሪም በቅርቡ በባህር ዳር ከተማ የተካሄደውን የብሪክስ የጥናት ተቋማት ምክክር ተከትሎ፣ ኢትዮጵያ በስብስቡ ውስጥ ያላትን የፖሊሲ ተፅዕኖ የማሳረፍ እና የአፍሪካን ድምጽ በዓለም አቀፍ መድረክ የማስተጋባት ሚና እያደገ መምጣቱን ይህ የቤጂንግ ፎረም ዳግም አረጋግጧል።
በሰለሞን ገዳ