በዓለማችን ግዙፍ ኢኮኖሚ ባላቸው በቻይና እና በአሜሪካ መካከል ያለው የንግድ ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት እና በ"ሰጥቶ መቀበል" መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ አስታወቁ።
ፕሬዝዳንቱ እንደገለጹት፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚደረግ ስትራቴጂካዊ ትብብር ለሁለቱም ወገኖች ብልፅግናን የሚያመጣ ሲሆን፣ ፍጥጫ ግን የሁለቱንም ሀገራት ብሔራዊ ጥቅም በእጅጉ የሚጎዳ ነው።
ዥንሁዋ ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የቻይና-አሜሪካ የንግድ ግንኙነት ተረጋግቶ መቀጠል ለሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች መሠረታዊ ፍላጎት መከበር ብቻ ሳይሆን፣ ለዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገትም የማይተካ ሚና ይጫወታል።
ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን አንጻራዊ ብልጫ በመጠቀም የሚያደርጉት የሁለትዮሽ የሸቀጦች ንግድ እርስ በርስ የሚደጋገፍና ለዓለም ገበያ መረጋጋት አይነተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑ ተመልክቷል።
ቻይና ሆን ብላ የንግድ ትርፍን እንደማታሳድድ የገለጸው ይኸው መረጃ፣ በአሁኑ ወቅት የሚታየው የንግድ ሚዛን ልዩነት ከአሜሪካ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሁኔታዎች እና ከዓለም አቀፍ የሥራ ክፍፍል የሚመነጭ የማይቀሬ ውጤት መሆኑን አስረድቷል።
ከሸቀጦች ንግድ በተጨማሪ በሀገራቱ መካከል ያለው የአገልግሎት ዘርፍ እና የሁለትዮሽ ኢንቨስትመንት ፈጣን ዕድገት እያሳየ ይገኛል።
የዓለማችን የኢኮኖሚ ምሰሶ የሆኑት ቻይና እና አሜሪካ የሚያደርጉት ንግድና ኢንቨስትመንት ለኩባንያዎችና ለሸማቾች ተጨባጭ ጥቅሞችን እያስገኘ ሲሆን፣ ይህም ትብብሩ በሁለቱም ወገኖች ዘንድ "አሸናፊ-አሸናፊ" የሆነ ውጤት እያመጣ መሆኑን የሚያረጋግጥ መሆኑ ተገልጿል።
በመሀመድ ፊጣሞ
#Economy #TradeRelations #XiJinping #GlobalGrowth