Search

የዲጂታል ዲፕሎማሲ አዲስ ምዕራፍ በኢትዮጵያ

ሰኞ ግንቦት 17, 2018 56

የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ገፅታ ለበርካታ አስርት ዓመታት በምዕራባውያን የዜና ተቋማት አማካኝነት ድህነትን፣ ቀውስን እና ጥገኝነትን በሚያጎሉ አሉታዊ ትረካዎች ተፅዕኖ ስር ቆይቷል።

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት የሀገራችን የኮሙኒኬሽን ሥነ-ምህዳር በዲጂታላይዜሽን የታገዘ አዲስ የገፅታ ግንባታ ስትራቴጂ እየተተገበረ ይገኛል።

ሀገራችን የተለመዱ የሕዝብ ግንኙነት ዘመቻዎችን ከመከተል ይልቅ ዘመኑን በዋጁ እና ውጤታማ በሆኑ የማኅበራዊ ሚዲያ ስልቶች ላይ አተኩራለች።

በርካታ ሚሊዮኖች የሚከተሏቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የኢትዮጵያን እውነተኛ ገፅታ በቀጥታ ለዓለም ሕዝብ ተደራሽ እያደረጉ ይገኛሉ።

ተፅዕኖ ፈጣሪዎቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዓይናቸውን ኢትዮጵያ ላይ ከመጣላቸው ባለፈ፣ የሚያስቧት ኢትዮጵያ እና ትክክለኛዋ ኢትዮጵያ የተለያዩ መሆናቸውን በተግባር እየመሰከሩ ነው።

ይህ አዲስ አካሄድ ባህላዊ የጂኦፖለቲካ በር ጠባቂዎችን በመዝለል የሀገራችንን የዕድገት ምኞት እና ታሪካዊ ሉዓላዊነት ለዓለም ለማሳየት አስችሏል።

ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች እና ያስመዘገቧቸው ስኬቶች

ማኅበራዊ ሚዲያን ለሀገር ገፅታ ግንባታ በመጠቀም ረገድ ኢትዮጵያ በርካታ ጥቅሞችን እያገኘች ነው።

ለዚህም ዋነኛው ማሳያ የአሜሪካው ታዋቂ የዩቲዩብ ቀጥታ አቅራቢ ዳረን ዋትኪንስ ጁኒየር (አይሾውስፒድ) በአዲስ አበባ ያደረገው የቀጥታ ሥርጭት ነው።

ይህ በአራት ሰዓት ከሃምሳ ሁለት ደቂቃ የተጠናቀቀው ሥርጭት በአህጉሪቱ ከፍተኛ የተመልካች ቁጥር ክብረ ወሰንን የሰበረ ነበር።

20 ሰዓታት ውስጥ 10 ሚሊዮን እይታዎችን ከማስመዝገቡም በላይ ሥርጭቱ በነበረበት ወቅት ብቻ 260 ሺህ በላይ አዳዲስ ሰብስክራይበሮችን አግኝቷል።

አይሾውስፒድ በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ላይ ያደረገው ስርጭት አዲሱን የአዲስ አበባን ለውጥ በትክክል ለዓለም ያሳየ ነበር።

ከሁሉም በላይ ደግሞ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ውስጥ በባዶ እግሩ በመጓዝ የኢትዮጵያን የጥንት አርበኞች ታሪካዊ ገድል ማክበሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ አዎንታዊ ምላሽን አስገኝቷል።

በቲክቶክ መድረክ ግንባር ቀደም የዜና ይዘት ፈጣሪ የሆነው ዲላን ፔጅ (ኒውስ ዳዲ) አዲስ አበባን እና የተለያዩ የሀገራችንን አካባቢዎች ጎብኝቶ ግርምቱን ለዓለም ሕዝብ አጋርቷል።

ዲላን ፔጅ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት በቲክ ቶክ ገጹ ላይ የለቀቀውን "ወደ ኢትዮጵያ ልሄድ ነው" ማስታወቂያ ብቻ 6 ሚሊዮን በላይ ተከታዮቹ ተመልክተውታል።

እንደ አራዳ ፓርክ ያሉ የመዝናኛ ቦታዎችን እና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን ተመልክቶ ለዓለም ሕዝብ አሰራጭቷል።

ችግኝ በመትከል እና የላቁ የቴክኖሎጂ ተቋማትን በመጎብኘት የሀገራችንን የአካባቢ ጥበቃ እና የሳይንሳዊ ዘመናዊነት ገፅታ ለዓለም አንጸባርቋል።

ሐረርን፣ ወንጪን፣ አፋርን እና ላሊበላን በመጎብኘትም የኢትዮጵያን ውብ ገጽታ 20 ሚሊዮን ገደማ ለሚሆኑ ተከታዮቹ አጋርቷል።

አንጋፋው የጉዞ ቪሎገር ድሩ ቢንስኪ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ሁለተኛው ተመራጭ የጉዞ መዳረሻው አድርጎ በመመደብ ላሊበላን፣ ድሬዳዋን፣ ሐረርን እና የኦሞ ሸለቆን ዓለም እንዲጎበኝ ጥሪ አቅርቧል።

እነዚህ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የሀገራችንን ታሪካዊ ጥንካሬ፣ የቴክኖሎጂ ፍላጎቷን እና የበለፀጉ ባህላዊ ሀብቶቿን ያቀናጀ ሁለገብ ማንነት በቀጥታ ለዓለም ተደራሽ አድርገዋል።

በዚህ የዲጂታል ዲፕሎማሲ ጉዞ ውስጥ ሌላው ትልቅ አሻራ ያሳረፈው ታዋቂው ጋናዊ የዩቲዩብ ይዘት ፈጣሪ ዎዴ ማያ (Wode Maya) ነው።

ዎዴ ማያ ኢትዮጵያን በጎበኘባቸው ሁለት ታሪካዊ አጋጣሚዎች የሀገራችንን እውነተኛ ገፅታ ለአፍሪካውያን እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማሳየት የፓን አፍሪካኒዝም መንፈስን በተግባር አሳይቷል።

በተለይም ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በአካል በመጎብኘት እና ግንባታውን በካሜራው በማስቀረት፣ ግድቡ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአጠቃላይ አፍሪካ ያለውን የኢኮኖሚ እና የትብብር ፋይዳ በስፋት አብራርቷል።

ይህ ዘገባው በምዕራባውያን ሚዲያዎች በግድቡ ዙሪያ ይነዙ የነበሩ የተዛቡ ትርክቶችን በማክሸፍ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ አየር መንገድን ስኬት፣ የሀገር በቀል ኢንዱስትሪዎችን እና የኢትዮጵያውያንን የእንግዳ ተቀባይነት ባህል በማጉላት ሀገራችን ያላትን እምቅ አቅም በተጨባጭ አሳይቷል።

የአፍሪካ ማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ ተቋማዊ ስኬት

ይህንን የትርክት ለውጥ ስትራቴጂ የበለጠ ተቋማዊ ለማድረግ ኢትዮጵያ በቅርቡ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ያስተናገደችው የመጀመሪያው የአፍሪካ ማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ ሌላው ትልቅ ስኬት ነው።

"ተፅዕኖ ፈጣሪነት ለተሻለች አፍሪካ" በሚል መሪ ቃል በተካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ 30 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ እና በጥምረት 321 ሚሊዮን ተከታዮች ያሏቸው 61 ታዋቂ የይዘት ፈጣሪዎች ተሳትፈዋል።

ይህም አዲስ አበባን የአፍሪካ ዲጂታል ትርክት መቆጣጠሪያ እና የፈጠራ ኢኮኖሚ ማዕከል አድርጓታል።

በምዕራባውያን ሚዲያዎች የሚሰራጩ አሉታዊ እና የተዛቡ ዘገባዎች አፍሪካን በየዓመቱ በቱሪዝም፣ በኢንቨስትመንት እና በብድር ወለድ 4.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያከስሯት በጉባኤው ተነስቷል።

እንደነዚህ ያሉ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን መጠቀም ይህንን የኢኮኖሚ ኪሳራ ለመቀልበስ እና የዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑም በግልጽ ታይቷል።

የከተማ መሠረተ ልማት እንደ ይዘት መፍጠሪያ መድረክ

ይህ የዲጂታል ገፅታ ግንባታ ስኬት ከአዲስ አበባ መዋቅራዊ ለውጥ ጋር ቀጥተኛ ትስስር አለው።

2016 . ጀምሮ ወደ ተግባር የገባው የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ፕሮጀክት በሁለት ምዕራፎች ውስጥ 132 ኪሎ ሜትሮችን በማካተት ዋና ዋና የከተማዋን ክፍሎች ሙሉ በሙሉ ቀይሯል።

መንግሥት እንደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ አንድነት ፓርክ፣ ወዳጅነት ፓርክ እና እንጦጦ ተፈጥሮ ፓርክ ያሉ ዘመናዊና ማራኪ የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎችን በመገንባት ከተማዋን ለዲጂታል ቀረጻ የተመቸች የይዘት መድረክ አድርጓታል።

ዓለም አቀፍ የይዘት ፈጣሪዎች በእነዚህ በተዋቡ ኮሪደሮች፣ በብስክሌት መንገዶች እና በሙዚቃ ፏፏቴዎች የታጀቡ ሥፍራዎች ላይ ሆነው ይዘቶችን በሚያስተላልፉበት ወቅት፣ ከተማዋ ያላትን ዘመናዊነት እና ውበት በማሳየት የቆዩ የድህነት እና የመሠረተ ልማት መውደም ትረካዎችን በተግባር ይሞግታሉ።

እዚህ ላይ ደግሞ የኖረው የኢትዮጵያውያን ባህል ሲታከልበት የጠለሸው የኢትዮጵያ ገጽታ ይፈካል፤ ዓለምም ትኩረቱን ወደ ኢትዮጵያ ያደርጋል፤ ይህ ደግሞ በተግባር እየተገለጠ ነው።

የዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እና የሩዋንዳ ማሳያ

በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ሀገራት ማኅበራዊ ሚዲያዎችን እና ታዋቂ ሰዎችን በመጠቀም የሀገር ገፅታቸውን ለመገንባት እና ቱሪዝምን ለማሳደግ ከፍተኛ ገንዘብ ይመድባሉ።

ለዚህም እንደ ትልቅ ማሳያ የምትወሰደው የምሥራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ሩዋንዳ ናት። ሩዋንዳ ሩዋንዳን ይጎብኙ (Visit Rwanda) የሚለውን የሀገር ገፅታ ግንባታ መልዕክት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስረፅ ለታዋቂው የእግር ኳስ ክለብ አርሴናል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ትከፍላለች።

በዚህም ምክንያት የክለቡ ተጫዋቾች ማሊያ እጅጌ ላይ እና በስታዲየም ማስታወቂያ ሰሌዳዎች ላይ ይህንን መልዕክት በማስቀመጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የክለቡን ደጋፊዎች በቀጥታ መድረስ ችላለች።

ይህ ዓይነቱ ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ የሚጠይቅ ስልት፣ ሀገራት ነባር የሚዲያ ማስታወቂያዎችን በመዝለል በቀጥታ ወደ ዓለም አቀፍ ታዳሚዎች ለመድረስ የሚጠቀሙበት መንገድ ነው።

ኢትዮጵያም በተመሳሳይ መልኩ ዓለም አቀፍ ዲጂታል ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን እና አህጉራዊ ጉባኤዎችን በከተማዋ በማስተናገድ ያሳካችው የገፅታ ግንባታ ስትራቴጂ የዚሁ ዘመናዊ የዲጂታል ዲፕሎማሲ አካል ተደርጎ ይወሰዳል።

በአጠቃላይ የዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉዞ፣ የኮሪደር ልማት መሠረተ ልማት እና የአህጉራዊ ዲጂታል ጉባኤዎች ጥምረት ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘመን ራሷን ለማስተዋወቅ የጀመረችው ስትራቴጂ ውጤታማ መሆኑን ያሳያል።

ይህንን የውጭ ገፅታ ግንባታ ስኬት ከሀገር ውስጥ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች ጋር በጥንቃቄ በማቀናጀት፣ ሀገራችን በዲጂታል ዓለም የትርክት የበላይነትን የማስከበር እና የቱሪዝም ፍሰቷን የማሳደግ ጉዞዋን በላቀ ደረጃ ማሳካት እንደምትችል የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በለሚ ታደሰ