Search

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ላይ መዋቅራዊ ማሻሻያ ሊደረግ እንደሚገባ ብሪክስ አስታወቀ

ሰኞ ግንቦት 10, 2018 93

በሕንድ አስተናጋጅነት በኒው ዴልሂ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የብሪክስ አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ፣ በዓለም አቀፍ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓቶች ላይ የቡድኑን የጋራ አቋም የሚያንጸባርቅ ባለ 63 አንቀጽ መግለጫ በማጽደቅ ተጠናቋል።

በሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ የተደረገው ይህ የጋራ መግለጫ፣ በአውሮፓውያኑ መስከረም 2026 ሕንድ በምትመራው የብሪክስ መሪዎች ጉባኤ ላይ ለሚነሱ ዋና ዋና አጀንዳዎችና ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ተግባራት መሠረት የጣለ መሆኑ ተገልጿል።

የብሪክስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተለይም በፀጥታው ምክር ቤት አሠራር ላይ አፋጣኝ መዋቅራዊ ማሻሻያ ሊደረግ እንደሚገባ በድጋሚ አረጋግጠዋል። ምክር ቤቱ ይበልጥ ዲሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ውጤታማ ውክልና እንዲኖረው ለማድረግ፣ የኢትዮጵያን ጨምሮ በማደግ ላይ ያሉ አገራት (Global South) በምክር ቤቱ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎና ድምፅ ሊጎለብት እንደሚገባ ሚኒስትሮቹ በጋራ መግለጫቸው ላይ በጥብቅ አሳስበዋል።

በሌላ በኩል፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምግብ ዋስትናንና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን ማረጋገጥ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፣ የ"ብሪክስ የእህል ልውውጥ" የንግድ መድረክን ለመመሥረት የተጀመረው ውጥን ይበልጥ እንዲጎለብትና ወደፊት ሌሎች የግብርና ምርቶችንና ሸቀጦችን እንዲያካትት ፍላጎታቸውን ገልጸዋል።

ሚኒስትሮቹ አያይዘውም በአካባቢው ማኅበረሰቦች ውስጥ የሚገኙ አነስተኛ አራሽ አርሶ አደሮች በምግብ ሥርዓት ውስጥ ያላቸውን የላቀ ሚና እውቅና ሰጥተዋል። የጋራ መግለጫው የዓለምን ብዝሃ ሕይወት ለመጠበቅ አገራት የቴክኖሎጂ ሽግግርና ልውውጥ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

በተለይም ካርቦንን በመምጠጥ፣ የአፈርና የውኃ ሀብትን በመጠበቅ ረገድ የሐሩር (ትሮፒካል) ደኖችን ጨምሮ የሁሉም የደን ዓይነቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፣ መሬት መጎስቆልንና በረሃማነትን መከላከል እንደሚገባና ብሪክስ ብርቅዬ እንስሳትን ለመጠበቅ የሚያደርገውን ጥረት አድንቋል።

በጤናው ዘርፍም ሚኒስትሮቹ በዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ማዕቀፍ ውስጥ ያለውን ትብብር ለማጠናከርና ፍትሐዊ፣ ተደራሽና ዘላቂ የጤና ሥርዓት ለመገንባት የተስማሙ ሲሆን፣ ከዚህ መደበኛ አሠራር በተጨማሪ እንደ ዲጂታል ጤና አጠባበቅና የኑክሌር ሕክምና ባሉ አዳዲስና ቅድሚያ በሚሰጣቸው የሕክምና ዘርፎች ላይ በትብብር ለመሥራት ያላቸውን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት ወይም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ለኢኮኖሚ ዕድገትና ለዘላቂ ልማት ከፍተኛ ዕድልና ማበረታቻ እንዳለው የገለጸው መግለጫው፣ በማደግ ላይ ያሉ አገራት የቴክኖሎጂ ባለቤት እንዲሆኑ፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን እንዲያገኙና የ-AI ግብዓቶችን በፍትሐዊነት ለመጠቀም በዚህ ዘርፍ የሚደረግ ዓለም አቀፍ ትብብር ወሳኝ መሆኑን አስምሮበታል።

የብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ የተካሄደው ከአጋር አገራት ተወካዮች ጋር በሰፊው መድረክ ሲሆን፣ ሚኒስትሮቹ እነዚህ አገራት ለስኬታማነቱ ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበው ይህ ዓይነቱ ተሳትፎ ዓለም አቀፍ ትብብርንና የአጋርነት መንፈስን እንደሚያጠናክር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በተጨማሪም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በትይዩ በሩሲያ ሞስኮ ከተማ 11ኛ ዓመታዊ ጉባኤውን እያካሄደ ያለውን የአዲሱ ልማት ባንክ (NDB) የአባልነት ማስፋፋት እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፉ በጋራ መግለጫቸው ማረጋገጣቸውን የኒው ዴልሂው ዘገባ ያመላክታል።

በሰለሞን ገዳ