Search

ብሔራዊ ዳታ - የማይበገር ሉዓላዊነት

ማክሰኞ ግንቦት 11, 2018 56

በዘመናዊው ዓለም ዳታ ወይም መረጃ የኃይል ምንጭ፣ የፖሊሲ አቅጣጫ መለኪያ እና የኢኮኖሚ ጥንካሬ ማረጋገጫ ሆኗል።

ብሔራዊ ዳታ፣ የአንድ ሀገር ዜጎች ማንነትን፣ የሀብት ክምችትን፣ የደኅንነት ምሥጢራትን፣ የማኅበራዊ አገልግሎቶችን እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን የሚያጠቃልል ሰፊ እና ስትራቴጂያዊ የዲጂታል ቋት ነው። 

ይህ መረጃ የሀገርን የልማት ሁኔታ የሚወስን፣ አደጋዎችን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል እና ለወደፊት ትውልድ የሚተላለፍ የዲጂታል ቅርጽ ያለው ብሔራዊ ሀብት ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ ሀገራት ዳታን እንደ ብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ እየቆጠሩት ነው። ለምሳሌ የአውሮፓ ኅብረት የጂ...አር (GDPR) መመሪያን በመቅረጽ የዜጎቹን መረጃ ከውጭ ኩባንያዎች ወረራ ለመጠበቅ የሚያስችል ጠንካራ የሕግ መጋረጃ ዘርግቷል።

ቻይና በበኩሏ የሳይበር ሉዓላዊነት መርሕን በመከተል፣ በሀገሯ የሚንቀሳቀሱ ኩባንያዎች መረጃን በሀገር ውስጥ ሰርቨሮች እንዲያከማቹ እና በብሔራዊ ሕግ እንዲመሩ በማድረግ፣ የዲጂታል ነፃነቷን በፅኑ መሠረት ላይ አቁማለች።

እነዚህ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት፣ ዳታን ለሦስተኛ ወገን አሳልፎ መስጠት የሀገርን ነፃነት ለስለላ፣ ለኢኮኖሚ ጫና እና ለዲጂታል ቅኝ ግዛት ማጋለጥ ነው።

ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የጀመረችው የመረጃ ሉዓላዊነት ጉዞ፣ ከታሪካዊ የጥገኝነት ሰንሰለት የመላቀቅ ቆራጥ እርምጃ ነው። ለረጅም ጊዜ የሀገራችንን ወሳኝ መረጃዎች በውጭ ሀገራት ሰርቨሮች ላይ ተቀምጠው የነበረ ሲሆን፣ ይህ ሁኔታ መንግሥት በነፃነት ውሳኔ የመስጠት አቅሙን ሲሸረሽር ቆይቷል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በተደጋጋሚ እንደሚያስገነዝቡት፣ የኢትዮጵያ መረጃዎች በራሷ ቁጥጥር ሥር መሆናቸው የብሔራዊ ክብር እና የሉዓላዊነት ምሽግ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር ይህንን እውነታ በመገንዘብ፣ የሀገር ውስጥ የክላውድ መሠረተ ልማት (National Cloud) ለመገንባት እና ብሔራዊ የመረጃ ማዕከላትን ለማዘመን እጅግ ደፋር እርምጃዎችን ወስዷል።

ይህ የቴክኖሎጂ ሽግግር ከውጭ መድረኮች ጥገኝነት በመውጣት፣ የኢትዮጵያን ዲጂታል ዕድሏን በራሷ እጅ ለመወሰን የተወሰደ ታሪካዊ እርምጃ ነው።

ኢትዮጵያ እየወሰደች ያለችው ይህ ቆራጥ እርምጃ በሁለት ዋና ዋና አቅጣጫዎች የላቀ ፋይዳ አለው።

አንደኛው፣ የዲጂታል ነፃነት ሲሆን፣ የሀገራችን የጤና፣ የፋይናንስ፣ የግብርና እና የደኅንነት መረጃዎች በራሳችን ሕግ እና ቁጥጥር ሥር እንዲሆኑ በማድረግ የውጭ ኃይሎች በዲጂታል መንገድ ተጽዕኖ እንዳያሳድሩብን ዋስትና ይፈጥራልናል።

ሁለተኛው፣ የዲጂታል ኢኮኖሚ ምኅዳር ነው። መረጃ በሀገር ውስጥ ሲከማች፣ ለሀገር ውስጥ የቴክኖሎጂ ስታርትአፖች ትልቅ በር ይከፈታል። መረጃው ሲኖር፣ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም ፈጠራዎችን መፍጠር እና የዜጎችን ኑሮ ማሻሻል ይቻላል።

የብሔራዊ ዳታ ሉዓላዊነት የነገዋ ኢትዮጵያ ብልጽግና ዋስትና ነው። ኢትዮጵያ መረጃዎቿን በራሷ መሠረተ ልማት ስታስተዳድር፣ የውጭ ተፅዕኖን በዲጂታል ጋሻ እየመከትን፣ የራሳችንን ዕጣ ፈንታ በራሳችን አዕምሮ እና መረጃ የምንወስንበት ብሩህ ጊዜ እውን እየሆነ ነው።

ይህ የዲጂታል ሉዓላዊነት ጉዞ፣ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ከአፍሪካ ተምሳሌት ለመሆን የምታደርገው የማይበገር ሩጫ ማሳያ ነው።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ