Search

ከአክራ እስከ አዲስ አበባ - የኢትዮጵያ ደማቅ አሻራ በአፍሪካ የነፃነት ታሪክ ውስጥ

ሰኞ ግንቦት 17, 2018 56

በየዓመቱ በፈረንጆቹ ግንቦት 25 በድምቀት የሚከበረው የአፍሪካ ቀን፣ አኅጉሪቱ ከቅኝ አገዛዝ ቀንበር ለመላቀቅ ያደረገችውን መራር ተጋድሎ እና ያስመዘገበችውን አንጸባራቂ ድል የምታስታውስበት ታሪካዊ ዕለት ነው።
ይህ የአፍሪካውያን የአንድነት፣ የነፃነት እና የሉዓላዊነት ምልክት የሆነው ቀን፣ ከጀርባው ረጅም እና መሥዋዕትነት የተሞላበት ታሪካዊ ጉዞ አለው።
በዚህ የነፃነት ጉዞ ውስጥ ደግሞ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት አለመያዟ እና ያስመዘገበችው የዓድዋ ድል ለአፍሪካውያን የነፃነት ንቅናቄ ትልቅ ተነሳሽነት በመፍጠር ረገድ ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል።
የአፍሪካ ቀን ታሪካዊ መሠረት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ በአኅጉሪቱ ከተቀጣጠለው የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግል ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት አለው።
መነሻውን እ.አ.አ በ1958 በጋና አክራ ከተማ ከተጠራው የመጀመሪያው የነፃ አፍሪካ ሀገራት ጉባኤ በማድረግ፣ ሚያዝያ 15 ቀን ይከበር የነበረው "የአፍሪካ ነፃነት ቀን"፣ በሒደት ጠንካራ ተቋማዊ መዋቅር ወደ መፍጠር ተሸጋግሯል።
በዚህም መሠረት እ.አ.አ ግንቦት 25 ቀን 1963 የ32 ነፃ አፍሪካ ሀገራት መሪዎች በአዲስ አበባ ተሰብስበው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ሲመሠርቱ፣ ቀኑ ወደ ግንቦት 25 ተቀይሮ "የአፍሪካ ቀን" ተብሎ በይፋ እንዲሰየም ተወስኗል።
በዚህ ሒደት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ብስለት ጎልቶ የወጣበት አጋጣሚ በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ የተፈጠረውን የርዕዮተ-ዓለም ክፍፍል ማስታረቅ መቻሏ ነው።
አኅጉሪቱ ወዲያውኑ ወደ አኅጉራዊ ፌዴሬሽን ትሸጋገር የሚለውን "የካዛብላንካ ቡድን" እና ውህደት በሒደት ይምጣ የሚለውን "የሞንሮቪያ ቡድን" በማቀራረብ ረገድ፣ የኢትዮጵያው ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።
ኢትዮጵያ ሚዛናዊ ረቂቅ አጀንዳ በማቅረብ የሁለቱንም ቡድኖች ፍላጎት በማስማማት፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተር ሊፈረም እና አዲስ አበባ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከል ልትሆን ችላለች።
ከዲፕሎማሲያዊ ጥረቷ ባሻገር፣ ኢትዮጵያ የነፃነት ታጋዮች ዋነኛ ደጀን ነበረች። የደቡብ አፍሪካውን የፀረ-አፓርታይድ ታጋይ ኔልሰን ማንዴላን ጨምሮ በርካታ የነፃነት ንቅናቄ መሪዎችን በወታደራዊ ሥልጠና እና በገንዘብ ደግፋለች።
ማንዴላ በኮልፌ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ማዕከል ሥልጠና ከመውሰዳቸውም በላይ፣ ኢትዮጵያዊ ስም እና ፓስፖርት ተሰጥቷቸው በኢትዮጵያውያን ጥበቃ ከግድያ ሴራ ተርፈው ለታላቅነት በቅተዋል።
በተጨማሪም ሀገራችን የአንጎላ፣ የሞዛምቢክ፣ የዚምባብዌ እና የናሚቢያ የነፃነት ታጋዮችን በማሠልጠን እና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነቷን ተወጥታለች።
አኅጉሪቱን ነፃ ለማውጣት በነበረው ሒደት ኢትዮጵያ ለአኅጉሪቱ ነፃነት በነበራት ቁርጠኝነት ምክንያት በራሷ ብሔራዊ ጥቅም እና ኢኮኖሚ ላይ ጭምር ከፍተኛ ጫና ደርሷል።
ከላይቤሪያ ጋር በመሆን አፓርታይድ ደቡብ አፍሪካን በዓለም አቀፍ የፍትሕ ፍርድ ቤት በመክሰስ ትልቅ አኅጉራዊ መሥዋዕትነት ከፍላለች።
ዛሬም ቢሆን ይህ የኢትዮጵያ ታሪካዊ መሠረት፣ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ልምድ እና ያላወላወለ አቋም ቀጥሏል።
የአፍሪካ ኅብረት በአዲሱ የዓለም ሥርዓት ውስጥ ይበልጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ እና ራሱን የቻለ ጠንካራ ተቋም እንዲሆን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሚናዋን ቀጥላለች።
በለሚ ታደሰ