Search

የቤጂንግ ጉባኤ፦ ትራምፕ እና ሺ የዓለምን መረጋጋት መልሕቅ ይጥሉ ይሆን?

ማክሰኞ ግንቦት 04, 2018 175

በቤጂንግ ታሪካዊው ቲያንአንመን አደባባይ ዙሪያ ለቀናት የደህንነት ጥበቃ ተጠናክሮ የቆየ ሲሆን፣ በዓለማችን ሁለት ኃያላን መሪዎች መካከል የሚደረገውን ታሪካዊ ጉባኤ ለመታደም የቻይና መናኸሪያ ደማቅ ድባብ ተጎናጽፋለች።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአውሮፓውያኑ 2017 ካደረጉት ጉብኝት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቤጂንግ የሚያደርጉት ይህ ጉዞ፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ለዓመታት ከታዩት እጅግ ወሳኝ የዲፕሎማሲ መድረኮች አንዱ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ጉብኝቱ ይፋዊ ውይይቶችንና የንጉሠ ነገሥት ቤተመቅደሶች ስብስብ የሆነውን "Temple of Heaven" መጎብኘትን የሚያካትት ሲሆን፣ ይህም በሁለቱ መሪዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማቀራረብ ያለመ ስልታዊ አካሄድ ተደርጎ ተወስዷል።

ይህ ጉባኤ በታላላቅ ዓለም አቀፍ አጀንዳዎች የተከበበ ነው። ላለፉት ወራት የዋሽንግተን ትኩረት በመካከለኛው ምስራቅና በአገር ውስጥ ጉዳዮች ላይ አርፎ የቆየ ቢሆንም፣ የቤጂንጉ ቆይታ ግን የዓለም አቀፍ ንግድ መጻኢ ዕድልን፣ የታይዋንን ወቅታዊ ሁኔታ እና በከፍተኛ ቴክኖሎጂዎች ላይ ያለውን የኃያላን ፉክክር ወደ ጠረጴዛው አምጥቷል።

የቻይናው ፕሬዝዳንት ጂንፒንግ የዓለም ኢኮኖሚ መረጋጋት ስለሚያስፈልጋቸው ይህ ስብሰባ ፍሬያማ እንዲሆን ጽኑ ፍላጎት አላቸው። በተለይም በኢራን ጦርነት ምክንያት የነዳጅ ዋጋ መጨመር በቻይና አምራቾች ላይ እያሳደረ ያለውን ጫና ለማቃለል፣ ቤጂንግ ከፓኪስታን ጋር በመሆን እንደ ሰላም አስከባሪ ሚና ለመጫወትና የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲመጣ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን እያደረገች ትገኛለች።

በንግድና በቴክኖሎጂው ዘርፍ የሚታየው ውጥረትም ሌላኛው የውይይቱ ምሰሶ ነው። ባለፈው ጥቅምት በደቡብ ኮሪያ ከተደረገው የሁለቱ መሪዎች ፊት ለፊት ግንኙነት በኋላ የረገበው የንግድ ጦርነት፣ አሁን ላይ ወደ አዲስ የትብብር ምዕራፍ ሊሸጋገር እንደሚችል ፍንጮች እየታዩ ነው።

ትራምፕ ቻይና የአሜሪካን የግብርና ምርቶች ግዢ እንድትጨምር ግፊት ሲያደርጉ፣ ቻይና ደግሞ በንግድ አሠራር ላይ የሚጣሉ ገደቦች እንዲላሉ ፍላጎቷን ታሳያለች።

እንደ ኒቪዲያ፣ አፕል እና ቦይንግ ያሉ ታላላቅ የንግድ ተቋማት መሪዎች ፕሬዝዳንት ትራምፕን አጅበው መጓዛቸውም፣ ጉብኝቱ ከፖለቲካዊ ፋይዳው ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ትስስሩን ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ያረጋግጣል።

የወደፊቱን ዓለም የሚወስነው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) እና የከፍተኛ ቴክኖሎጂ ፉክክርም በሁለቱ መሪዎች መካከል ጥበብ የተሞላበት ድርድርን ይፈልጋል።

ቻይና ለዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች አስፈላጊ የሆኑትን ብርቅዬ ማዕድናት በበላይነት የምታቀርብ በመሆኗ፣ ይህንን አቅሟን ከአሜሪካ ዘመናዊ ቺፕስ ጋር የምትለዋወጥበት ስምምነት ላይ ሊደረስ እንደሚችል ይገመታል።

ምንም እንኳን ጉብኝቱ አጭር ቢሆንም፣ በሁለቱ መሪዎች መካከል የሚደረገው ይህ ግንኙነት ለሚቀጥሉት ዓመታት የዓለምን ጂኦ-ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አቅጣጫ የሚወስን የዲፕሎማሲ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል።

በሰለሞን ገዳ