የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና የቴክኖሎጂ ልዕልና ጉዞ ከራዕይ ባለፈ ወደ ተጨባጭ ማዕቀፍ መሸጋገሩን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ገለጹ።
ዋና ዳይሬክተሩ ይህን የገለጹት በኢንስቲትዩቱ፣ በዩኔስኮ (UNESCO) እና በአውሮፓ ኅብረት ትብብር የተዘጋጀውን ከፍተኛ የፖሊሲ ምክክር መድረክ በንግግር በከፈቱበት እና ሀገራዊ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዝግጁነት ምዘና (RAM) ሪፖርትን ባቀረቡበት ወቅት ነው።
ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በንግግራቸው፣ መድረኩ በሀገራችን የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ምርምር እና ልማት ሥራዎችን ይበልጥ ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዝግጁነት ምዘና ሪፖርቱም ተራ ግምገማ ሳይሆን "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂን ለማሳካት ወደፊት ለሚወሰዱ ስልታዊ እርምጃዎች ጽኑ መሠረት የሚጥል ፍኖተ-ካርታ መሆኑን አብራርተዋል።
"አፍሪካ ከእንግዲህ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ብቻ ሳትሆን ፈጣሪ ጭምር ናት" ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ በዘርፉ ቀዳሚ ለመሆን በምታደርገው ጥረት ያካበተችውን ተቋማዊ ልምድ እና ዕውቀት ለአፍሪካውያን ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።
#Ethiopia #EU #UNESCO #Africa #technology #artificialintelligence #EBC