Search

የአፍሪካ ድምፅ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ጉልህ ስፍራ አግኝቷል - የአፍሪካ ኅብረት

ሰኞ ግንቦት 17, 2018 49

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማሕሙድ ዓሊ ዩሱፍ፣ 63ኛው የአፍሪካ ቀንን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሊቀመንበሩ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ይህ ዕለት አህጉራችን ለአንድነት፣ ለነፃነት፣ ለክብር እና ለልማት የምታደርገውን የጋራ ጥረት የምታድስበት ታሪካዊ ምዕራፍ ነው ብለዋል።
የዘንድሮው የአፍሪካ ቀን ‘የ63 ዓመታት አንድነት፣ ውህደት እና ልማት’ በሚል መሪ ቃል እየተከበረ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ አፍሪካውያን የምንፈልጋትን አፍሪካ ለመገንባት እና ለአጀንዳ 2063 ስኬት ያላቸውን የማይናወጥ ቁርጠኝነት ዳግም የሚያረጋግጡበት መሆኑን አስታውቀዋል።
የአፍሪካ ቀን የጋራ ቅርሳችን ማክበሪያ ብቻ ሳይሆን፣ “እኔ ያለሁት እኛ ስላለን ነው” በሚለው የኡቡንቱ መንፈስ እየተመራች አፍሪካ ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን በመቅረጽ ረገድ የምታደርገውን እያደገ የመጣ ሚና እውቅና መስጫ ነውም ብለዋል።
አህጉራችን እርግጠኛ ባልሆነው የዓለም ሁኔታ ውስጥ አንድነትን፣ ትብብርን እና የጋራ ሰብአዊነትን በግንባር ቀደምትነት ማራመዷን እንደምትቀጥልም አረጋግጠል።
በተለይም ባለፈው ዓመት የአፍሪካ ድምፅ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ጉልህ ስፍራ ማግኘቱን የገለጹት ሊቀመንበሩ፣ አፍሪካ በቡድን 20 (G20) ውስጥ ያገኘችው ቋሚ አባልነት ታሪካዊ እርምጃ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህ አባልነት አፍሪካ በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ሙሉ በሙሉ እንድትሳተፍ የሚያስችላት ሲሆን፣ በሰላም፣ በአየር ንብረት፣ በምግብ ዋስትና፣ በንግድ፣ በጤና እና በዘላቂ ልማት ላይ ለሚደረጉ ዓለም አቀፍ መፍትሔዎች ትርጉም ያለው አስተዋፅኦ እንድታበረክት በር የከፈተ መሆኑን አስረድተዋል።
የአፍሪካ ኅብረት የሕዝቦቹን ፍላጎት ማሳካት የሚችል ጠንካራ፣ ይበልጥ ውጤታማ እና ምላሽ ሰጪ ተቋም ለመሆን ተቋማዊ ማሻሻያዎችን በተከታታይ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ በመልዕክቱ ተመልክቷል።
የዘንድሮው የአፍሪካ ኅብረት የዓመቱ መሪ ቃል ‘የአጀንዳ 2063 ግቦችን ለማሳካት ዘላቂ የውኃ አቅርቦት እና አስተማማኝ የንፅህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ’ የሚል መሆኑን ያስታወሱት ሊቀመንበሩ፣ ይህም የውኃ ዋስትና፣ የአየር ንብረት መቋቋም አቅም፣ የሕዝብ ጤና እና ዘላቂ ልማት ለአፍሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ወሳኝ መሠረቶች መሆናቸውን የሚያጎላ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በዮናስ በድሉ