Search

ከአክራ እስከ አዲስ አበባ፡ የኢትዮጵያ ደማቅ አሻራ በአፍሪካ የነጻነት ታሪክ ውስጥ

ሰኞ ግንቦት 17, 2018 40

በየዓመቱ ግንቦት 25 ቀን በድምቀት የሚከበረው የአፍሪካ ቀን፣ አህጉሪቱ ከቅኝ አገዛዝ ቀንበር ለመላቀቅ ያደረገችውን መራር ተጋድሎ እና ያስመዘገበችውን አንጸባራቂ ድል የምታስታውስበት ታሪካዊ ዕለት ነው።

ይህ የአፍሪካውያን የአንድነት፣ የነጻነት እና የሉዓላዊነት ምልክት የሆነው ቀን፣ ከጀርባው ረጅም እና መሥዋዕትነት የተሞላበት ታሪካዊ ጉዞ አለው።

በዚህ የነጻነት ጉዞ ውስጥ ደግሞ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት አለመያዟ እና ያስመዘገበችው የዓድዋ ድል ለአፍሪካውያን የነጻነት ንቅናቄ ትልቅ ተነሣሽነት በመፍጠር ረገድ ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል።

የአፍሪካ ቀን ታሪካዊ መሠረት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ በአህጉሪቱ ከተቀጣጠለው የጸረ-ቅኝ አገዛዝ ትግል ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት አለው።

መነሻውን .. 1958 በጋና አክራ ከተማ ከተጠራው የመጀመሪያው የነጻ አፍሪካ ሀገራት ጉባኤ በማድረግ፣ ሚያዝያ 15 ቀን ይከበር የነበረው "የአፍሪካ ነጻነት ቀን" በሂደት ጠንካራ ተቋማዊ መዋቅር ወደ መፍጠር ተሸጋግሯል።

በዚህም መሠረት .. ግንቦት 25 ቀን 1963 32 ነጻ አፍሪካ ሀገራት መሪዎች በአዲስ አበባ ተሰብስበው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ሲመሰርቱ፣ ቀኑ ወደ ግንቦት 25 ተቀይሮ "የአፍሪካ ቀን" ተብሎ በይፋ እንዲሰየም ተወስኗል።

በዚህ ሂደት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ብስለት ጎልቶ የወጣበት አጋጣሚ 1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ የተፈጠረውን የርዕዮተ-ዓለም ክፍፍል ማስታረቅ መቻሏ ነው።

አፍሪካ ወዲያውኑ ወደ አህጉራዊ ፌዴሬሽን ትሸጋገር የሚለውን "የካዛብላንካ ቡድን" እና ውህደት በሂደት ይምጣ የሚለውን "የሞንሮቪያ ቡድን" በማቀራረብ ረገድ፣ የኢትዮጵያው ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።

ኢትዮጵያ ሚዛናዊ ረቂቅ አጀንዳ በማቅረብ የሁለቱንም ቡድኖች ፍላጎት በማስማማቷ፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተር ሊፈረም እና አዲስ አበባ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከል ልትሆን ችላለች።

ከዲፕሎማሲያዊ ጥረቷ ባሻገር፣ ኢትዮጵያ የነጻነት ታጋዮች ዋነኛ ደጀን ነበረች። የደቡብ አፍሪካውን የጸረ-አፓርታይድ ታጋይ ኔልሰን ማንዴላን ጨምሮ በርካታ የነጻነት ንቅናቄ መሪዎችን በወታደራዊ ሥልጠና እና በገንዘብ ደግፋለች።

ማንዴላ በኮልፌ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ማዕከል ሥልጠና ከመውሰዳቸውም በላይ፣ ኢትዮጵያዊ ስምና ፓስፖርት ተሰጥቷቸው በኢትዮጵያውያን ጥበቃ ከግድያ ሴራ ተርፈው ለታላቅነት በቅተዋል።

በተጨማሪም ሀገራችን የአንጎላ፣ የሞዛምቢክ፣ የዚምባብዌ እና የናሚቢያ የነጻነት ታጋዮችን በማሰልጠን እና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነቷን ተወጥታለች።

አፍሪካን ነጻ ለማውጣት በነበረው ሂደት ኢትዮጵያ ለአህጉሪቱ ነጻነት በነበራት ቁርጠኝነት ምክንያት በራሷ ብሔራዊ ጥቅም እና ኢኮኖሚ ላይ ጭምር ከፍተኛ ጫና ደርሷል።

ከላይቤሪያ ጋር በመሆን አፓርታይድ ደቡብ አፍሪካን በዓለም አቀፍ የፍትሕ ፍርድ ቤት በመክሰስ ትልቅ አህጉራዊ መሥዋዕትነት ከፍላለች።

ዛሬም ቢሆን ይህ የኢትዮጵያ ታሪካዊ መሠረት፣ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ልምድ እና ያላወላወለ አቋም ቀጥሏል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት በአዲሱ የዓለም ሥርዓት ውስጥ ይበልጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ እና ራሱን የቻለ ጠንካራ ተቋም እንዲሆን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሚናዋን ቀጥላለች።

በለሚ ታደሰ

#AfricaDay