ሕፃኗ ከመወለጃ ጊዜዋ ቀድማ በመወለዷ፣ ኪሎዋ ከሚጠበቀው በታች ሆኗል። ይህም በሕይወት ለመቆየት አስጊ እንደሆነ ይገለጻል። በዚህ ምክንያት የሕፃኗ ቤተሰቦች በጭንቀት ተውጠዋል።
ከዚህ ቀደም መሰል ሕፃናትን ከሞት የታደጉት እነ ዶ/ር ሚሼል፣ የዚህችንም ሕፃን ሕይወት ለማትረፍ ብዙ ለፍተዋል። ደግነቱኝ የዶ/ር ሚሼልና ባልደረቦቻቸው ልፋት መና አልቀረም፣ ከሳምንታት የልዩ ክትትል ሕክምና በኋላ የሕፃኗ የመኖር ተስፋ ለምልሟል።

ዶ/ር ሚሼል ዬትስ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ወላይታ ዞን፣ ሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል የሕፃናት ሕክምና ክፍል በበጎ ፈቃደኝነት በማገልገል ላይ ያሉ አሜሪካዊት የሕፃናት ሕክምና ስፔሻሊስት ናቸው። ላለፉት 12 ዓመታት በሆስፒታሉ ያገለገሉት ባለሙያዋ ተሞክሯቸውን አካፍለውናል።
ዶ/ር ሚሼል እንዳጫወቱን፣ 700 ግራም ብቻ ሆና የተወለደችው ሕፃን በሆስፒታሉ በተደረገላት ከፍተኛ ክትትልና እንክብካቤ በቅርቡ ከጨቅላ ሕፃናት ማቆያ (Incubator) ወደ እናቷ እቅፍ የተሸጋገረች ሲሆን፣ በጥሩ ጤንነት ላይ ትገኛለች።
ይህን መሰል የሕክምና ተዓምር ለእነ ዶ/ር ሚሼል የየዕለት ሥራ አካል ነው። የሚገርመው፣ እርሳቸውን ጨምሮ በሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል የሚያገለግሉ ሁሉም ዓለም አቀፍ ሠራተኞች ለአገልግሎታቸው ከሆስፒታሉም ሆነ ከሀገር ምንም ዓይነት ክፍያ አይቀበሉም።
የዕለት ተዕለት ኑሯቸው የሚደገፈው በትውልድ ሀገራቸው ከሚገኙ ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ከአብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች በሚደረግላቸው የገንዘብ ድጋፍ (donation) ነው።

ከሶስት ልጆቻቸው ሁለቱን በኢትዮጵያ የወለዱት አሜሪካዊቷ በጎ ፈቃደኛ ሐኪም፣ በሙያቸው ኢትዮጵያውያንን እያገለገሉ፣ የሕጻናትና እናቶችን ሕይወት ከሞት እየታደጉ ይገኛሉ።
በዶ/ር ሚሼል እና የሙያ አጋሮቻቸው ነፃ የሕክምና አገልግሎት አማካኝነት፣ የመክፈል አቅም የሌላቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን ታክመው ድነዋል። ይህን ማየት ሁሉንም ድካም የሚያስረሳ ትልቅ በረከት መሆኑን ዶ/ር ሚሼል በእርካታ ይገልጻሉ።
ከትውልድ ሀገር ርቆ መኖር፣ የቤተሰብ አባል ሲታመም በቅርብ አለመገኘት እንዲሁም በሠርግና ልቅሶ አለመታደም ከባድ ቢሆንም፣ ፈጣሪ ለዚህ አገልግሎት እንደጠራቸውና ፍላጎታቸውን ሁሉ እርሱ እንደሚያሟላላቸው በጽኑ ያምናሉ።

ይህ ዓይነቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሆስፒታሉ ለኅብረተሰቡ የሚያቀርበውን የሕክምና አገልግሎት በተመጣጣኝ ክፍያ ለማቅረብና አቅመ ደካሞችን ለመርዳት ትልቅ ዕድል ፈጥሯል ያሉን የሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኤፍሬም ገብረሥላሴ ናቸው።
ሆስፒታሉ የላቀ የሕክምና አገልግሎት መስጠት፣ ብቁ የሕክምና ባለሙያዎችን ማፍራት እና ከፍሎ የመታከም አቅም የሌላቸውን ማገዝን ዋነኛ ዓላማዎቹ አድርጎ መነሳቱን ገልጸዋል።
ሆስፒታሉ ዶ/ር ሚሼልን የመሳሰሉ በጎ ሰዎችን በማሰባሰብ እና በየዓመቱ እስከ 40 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ ከመላው ኢትዮጵያ ለሚመጡ የመክፈል አቅም የሌላቸው ታካሚዎች ነጻ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
በሲሳይ ደበበ
#Ethiopia #SoddoChristianHospital #CommunityService # DrMichelleYates