ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በሞጆ ከተማ የተገነባውን የግራንዴር ሴራሚክ ማምረቻ ፋብሪካን መርቀዋል።
በግራንዴር ሴራሚክ ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተገነባው ፋብሪካ፣ መሠረት ልማቱ በ300 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ፣ የዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ የሴራሚክ እና የፖርሲሌን ንጣፎች ማምረቻ ፋብሪካ መሆኑን እና ከዕቅድ እና መሬት ዝግጅት እስከ ሙሉ ሥራ ማስጀመር የወሰደው ጊዜ ዘጠኝ ወራት ብቻ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታውቋል።

በአሁኑ ወቅት 60x60 የሴራሚክ ንጣፎችን በስፋት ማምረት የጀመረው ይህ ፋብሪካ፤ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ የምርት ዓይነቶቹን በማስፋት የ80x80፣ 60x120፣ 70x140 እና 80x160 መጠን ያላቸውን የንጣፍ ዓይነቶች እንዲሁም የአውሮፓን የጥራት ደረጃ ያሟሉ የፖርሲሌን ምርቶችን ማቅረብ እንደሚጀምር ይጠበቃል።
ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ መዋዕለ-ነዋይ የወጣበት ይህ ፋብሪካ፣ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ሽግግር ጉዞ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ያመላከተ ክንውን መሆኑን ነው ጽ/ቤቱ ያስታወቀው።

ለፋብሪካው ምርት የሚያስፈልጉት ጥሬ ዕቃዎች 80 በመቶ የሚሆነው ከፋብሪካው በ100 ኪሎ ሜትር ክበብ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፤ ይህም ሙሉ በሙሉ የተቀናጀና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር የተሳሰረ የአቅርቦት ሰንሰለት ፈጥሯል።
ኢትዮጵያ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ባሳለፍናቸው ዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ ከ4.85 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማዳን በቻለችበት በዚህ ወቅት፣ የግራንዴር ሴራሚክ መከፈት የውጭ ምርት ጥገኝነትን የሚቀንስ ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ እንድትሆን የሚያስችላትም ጭምር ነው ሲል ገልጿል።