ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምሥራቅ ሸዋ ዞን ሞጆ ከተማ የተገነባውን የግራንዴር ሴራሚክ ፋብሪካ ዛሬ መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ "ክውጭ ድንጋይ ተሸክመን በማምጣት ሀገር መለወጥ አንችልም፤ ከውጭ የሚገቡ የግንባታ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም" ሲሉ አስገንዝበዋል።

ከትናንት ጀምሮ በምሥራቅ ሸዋ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር የግብርና እና የልማት እንቅስቃሴዎችን መመልከታቸውን ጠቁመዋል።
ማኅበረሰቡ በዶሮ እና በወተት ሀብት ልማት ላይ ያለውን አመለካከት በመቀየር፣ በቀን በሚሊዮን የሚቆጠሩ እንቁላሎችን እና ከፍተኛ የወተት ምርት ማምረት እንደሚቻል እና ከዚህ የሚገኘው ገቢ ከማንኛውም ፋብሪካ ከሚገኝ ገቢ እንደማያንስ አብራርተዋል።
እንደ ሀገር የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማሳካትም የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ማምረት ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውበታል።
የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ ገበያውን በማረጋጋት ረገድ ትልቅ ሚና እንደተጫወተ ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንን ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ የማስፋፊያ ሥራውን በሚቀጥሉት ከሦስት እስከ አራት ወራት ውስጥ እንደሚያጠናቅቅ ገልጸዋል።
በተያያዘም በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘው የብረታ ብረት ፋብሪካ ለግንባታው ዘርፍ ትልቅ አቅምና የምሥራች መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዛሬ በሞጆ የተመረቀው ፋብሪካ በዘጠኝ ወራት ውስጥ የተገነባ መሆኑን አድንቀው፣ ጠንክሮ ከተሠራ ማንኛውንም ታላቅ ተልዕኮ ማሳካት እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል።
"የጀመርነውን ለምን ከዳር አናደርስም? የተማሩ ወጣቶች ለምን ሥራ ፈትተው ይውላሉ?" ለሚሉት ጥያቄዎች መሠረታዊ የችግሩን ምንጭ መመርመር እና መፍታት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች የሀገር ሽማግሌዎችን እና የአባ ገዳዎችን ምክር በመስማት፣ ከጎጠኝነት እና ከመከፋፈል ወጥተው ለሰላም እና ለአንድነት በጋራ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በለሚ ታደሰ