Search

የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሌሎች የምክክር ሂደቶች በምን ይለያል?

ሰኞ ሰኔ 15, 2018 52

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሀገራዊ ምክክሩን ለማስተባበር ሥራውን ሲጀምር በስትራቴጂያዊ ዕቅዱ ካስቀመጣቸው ምሰሶዎች አንዱና ዋነኛው አጀንዳ የማሰባሰብ፣ የመለየት ብሎም የመቅረፅ ተግባር እንደነበር ይታወቃል፡፡

በተጨማሪም ኮሚሽኑ በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን እና ኃላፊነት መሠረት አጀንዳን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት በማሰባሰብ እንዲሁም በሂደቱ የሚሳተፉ ተሳታፊዎችን በመለየት የምክክር ሂደቱን ሲያስተባብር ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ኮሚሽኑ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍን በማጠናቀቅ ወደ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤው እየተንደረደረ ይገኛል፡፡

ነገር ግን ኮሚሽኑ በቅርቡ የሚያስተባብረው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ እስካሁን ከተደረገው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት በምን እንደሚለይ ማወቁ ጠቃሚ ነው፡፡ ኮሚሽኑ አጀንዳን በሰፋፊ ሕዝባዊ ውይይቶች ያሰባሰበበት የምክክር ሂደት የሚከተሉት ቁልፍ ባሕርያት ነበሩት፡፡

👉ባለድርሻ አካላት እንደ ሀገር ያልተግባባንባቸውን እጅግ መሠረታዊ የሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች በውይይት በማዳበር ለኮሚሽኑ አስረክበዋል፤

👉 የብዙ ባለድርሻ አካላት ሕመሞች፣ ሥጋቶች፣ ምኞቶች እና ተስፋዎች በአጀንዳ መልክ ቀርበዋል፤

👉 በሂደቱ ኮሚሽኑ ለምክክሩ ሂደት የሚጠቅሙ እጅግ በርካታ ግብዓቶችን ሰብስቧል፤

👉 በአንጻራዊነት የተሳታፊዎችን ምቾት ከግምት ውስጥ በማስገባት ለተሳታፊዎች ቅርብ ናቸው ተብለው በሚታሰቡ ቦታዎች የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ተከናውኗል፤

👉 በሕዝባዊ ውይይት አጀንዳን የመሰብሰብ ሥራ ብቻውን ሁለት ዓመታትን ፈጅቷል፡፡

በአጠቃላይ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤው መካሄድ እንደ ቅድመ ሁኔታ በማገልገል የራሱን ከፍተኛ ሚና መጫወቱ ቢታወቅም የሀገራዊ ምክክር ጉባኤውን የማይተካ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡

በመሆኑም የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው፦

👉 የሀሳብ ነፃነትን እና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ማዕከል በማድረግ የባለድርሻ አካላት ወኪሎች በኮሚሽኑ ተቀርፀው በቀረቡ የአጀንዳ ሀሳቦች ላይ መግባባት ላይ ለመድረስ የሚመካከሩበት ጥንቃቄ የተሞላው የምክክር ሂደት ነው፡፡

👉 በምክክር ሂደቱ መግባባት በተደረሰባቸው ሀሳቦች ላይ በመመርኮዝ ምክረ-ሀሳቦች እና የተለያዩ አማራጮች የሚዘጋጁበት ሂደት ነው፡፡

👉 መርሃ-ግብሩ በመዲናችን አዲስ አበባ ይከናወናል፡፡

👉 መርሃ-ግብሩ በየቦታው በተደረጉ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፎች በተሰብሳቢዎች በተመረጡ ተወካዮች ይከናወናል፡፡

👉 መርሃ-ግብሩ ከ4000 በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙበት ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን