Search

ታላቁን ርዕይ ታሳቢ ያደረገው የኢፌዴሪ የመደመር መንግሥት አወቃቀር

ዓርብ መስከረም 29, 2019 67

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት  ይፋ ያደረጉት አዲስ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አወቃቀርና የካቢኔ ሹመት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁ ይታወሳል።

ይህ የአዲስ መንግሥት ምስረታ ባለፈው ዓመት በወርሃ ግንቦት በተደረገው ጠቅላላ ምርጫ የተሰጠ ሕዝባዊ አደራን ለመወጣትና ዘመን ተሻጋሪ ተቋማትን ለመገንባት የሚያስችል ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።

በተለይም ያለፉት 5 ዓመታት የተከናወኑ የልማት እና የሪፎርም ሥራዎች ከከፍታቸው ዝቅ እንዳይሉ ለማድረግ ጠንካራ ተቋማትና ብቁ አመራሮች ወሳኝ ናቸው።

በዚሁ መሠረት ከነባር ሚኒስትሮች በተጨማሪ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት፣ ኤጀንሲዎችና ኮርፖሬሽኖች በዴኤታነትና በኃላፊነት ሲያገለግሉ የቆዩ ወጣት አመራሮች ወደፊት እንዲመጡ ተደርጓል።

በአዲሱ ካቢኔ አወቃቀር ከታዩ ዋና ዋና ለውጦች መካከል የሴቶች ተሳትፎ አንዱ ነው። ከዚህ ቀደም የነበረውን የሴቶች ተሳትፎ ይበልጥ በማሻሻል 9 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በሴቶች እንዲመሩ መደረጉ የመደመር መንግሥት ለሴቶች ተሳትፎ የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ነው።

በዚህም የሚፈለገውን ሀገራዊ ለውጥ ለማምጣት ሴቶችን በውሳኔ ሰጪነት በስፋት ማሳተፍ አስፈላጊ መሆኑ የተንጸባረቀበት ነው።

ተለዋዋጭ በሆነው ቀጣናዊና ዓለም አቀፍ ጂኦፖለቲካ ውስጥ ኢትዮጵያ በውጤታማ ዲፕሎማሲና በሰጥቶ መቀበል መርህ አሸናፊ ሆና እንድትወጣ እየተሠራ ሲሆን፤ የተሰየሙት አመራሮች ሕግንና ሥርዓትን መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ዝግጁ ሆነዋል።

ሹመት የድሎት ወንበር ሳይሆን ሕጋዊ እና ማህበራዊ ኃላፊነት እንዲሁም ትልቅ ሸክም ነው። በመሆኑም የተሰጡት ሹመቶች ከግለሰባዊ ትስስር የጸዱ፣ ንጹህ ጀርባ ያላቸው እንዲሁም የፀረ-ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉን አጠናክረው ማስቀጠል የሚችሉ መሆናቸው ተረጋግጧል።

በጥቅሉ የኢፌዴሪ የመደመር መንግሥት አወቃቀር ኢትዮጵያ እአአ እስከ 2050 የያዘችውን ታላቅ ሀገራዊ ርዕይ እውን ለማድረግ የሚያስችል መሠረት የሚጥል ነው።

በሔዋን ጌታቸው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: