ከአዲስ አበባ ወደ መቐለ የአውሮፕላን በረራ አገልግሎት እንደገና በመጀመሩ በጣም ተደስተናል አሉ አየር መንገዱ ተጠቃሚዎች።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀደም ሲል ጥቅምት 1 ቀን 2019 ዓ.ም ወደ መቐለ ከተማ በረራ እንደሚጀምር ባወጣው ማስታወቂያ መሠረት መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎቱን ዛሬ በይፋ ጀምሯል።
በዚህም መሠረት ከአዲስ አበባ የተነሳው የአየር መንገዱ አውሮፕላን ዛሬ ማለዳ በመቐለ ከተማ አልኡላ አባ ነጋ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አርፏል።
የአገልግሎቱን መጀመር ተከትሎም በርካታ የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች በአውሮፕላን ማረፊያው በመገኘት የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ ገልጸዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች እና ሌሎችም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ዜጎች የትራንስፖርት አገልግሎት እንደገና በመጀመሩ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እና ልማትን ለማፋጠን ያለውን ቁርጠኛ አቋምና ተግባራዊ ርምጃዎችን በግልጽ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ መጀመሩ በክልሉ የነዋሪዎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ እንደሚያፋጥን ተናግረዋል።
አቶ አሸናፊ ጸጋዬ እንዳሉት፤ ለሥራ ጉዳይ ወደ መቐለ በሄዱበት ወቅት በረራው በመቋረጡ ምክንያት ለችግር ተዳርገው ቢቆዩም አሁን አገልግሎቱ በመጀመሩ ትልቅ ደስታ ተሰምቷቸዋል፤ ተስፋቸው ለምልሟል።
የአየር መንገዱ የበረራ አገልግሎት መጀመር የትግራይ ሕዝብ ከነበረበት ሁለገብ ችግር እንዲወጣ ከሚያግዙ አስፈላጊ እርምጃዎች አንዱ መሆኑንም ገልጸዋል።
ክልሉ ለተለያዩ መሠረታዊ ቁሳቁሶች እጥረት ተጋልጦ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ አሸናፊ፤ የፌዴራል መንግሥት አሁን የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ በመቀጠል በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንደሚያጸና እምነታቸውን ገልጸዋል።
አቶ ናትኤል ሰለሞን በበኩላቸው፤ የበረራ አገልግሎቱ ዳግም በመጀመሩ እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አክሎም የትግራይ ሕዝብ ሰላም ወዳድ ሕዝብ መሆኑን በመግለጽ፤ የተጀመረው አበረታች የበረራ አገልግሎት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነት እንዳለው መናገሩን ኢዜአ ዘግቧል።
አቶ ሃድራት ኮት የበረራ አገልግሎቱ ዳግም በመጀመሩ የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ ገልጸው፤ ይህም ለክልሉ ሕዝብ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
#የመደመርመንግሥት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: