የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል በሕገ ወጡ ህወሓት ምክንያት የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን በፍጥነት በመመለስ እና የሰብአዊ እርዳታዎችን ያለምንም መዘግየት ለተቸገሩ ወገኖች በማዳረስ የሰላም እና የልማት ዋልታነቱን በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል።
ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል የትግራይን ሕዝብ እንደ መያዣ አድርጎ በመጠቀም የኢትዮጵያን ሀብት እና ጥሪት ሲመዘብር የቆየው ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን፣ በሕዝብ ቁጣ ከማዕከላዊ ሥልጣን ሲወገድ ዞር ብሎ አይቶት ወደማያውቀው የትግራይ ሕዝብ ጉያ ውስጥ ተወሸቀ።
ከአምስት ዐሥርት ዓመታት በፊት በነበረው የኋላቀር ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ታስሮ የቀረው ይህ ስብስብ፣ የራሱን የሥልጣን ጥም ለማርካት ሲል የትግራይን ወጣት ላልተገባ እና አላስፈላጊ ጦርነት ሲማግድ ቆይቷል።
የፌዴራል መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ ደኅንነት እና ለኢትዮጵያ ሰላም ሲል ባለፉት ዓመታት እጅግ ከፍተኛ የሆነ የትዕግሥት መንገድ ቢከተልም፣ ቡድኑ ግን የጥፋት መንገዱን በመምረጥ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከማደከሙ በላይ የወጣቱን ሕይወት ለቀጣይ እሳት ገብሯል።
የመንግሥት ጽኑ የሰላም ፍላጎት በፕሪቶሪያው ስምምነት አማካኝነት ክልሉ የሰላም አየር እንዲተነፍስ እና ወደ ነበሩበት መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲመለስ ትልቅ ዕድል ፈጥሮ ነበር።
ነገር ግን ሰላምን እንደ ሕመም የሚቆጥረው ይህ ቡድን የተሰጠውን የሰላም አማራጭ ገሸሽ በማድረግ ለቀጣይ ጦርነት ሲዘጋጅ ከርሟል።
የክልሉን ውስን ሀብት ለጥፋት ዓላማ በመመዝበር፣ አዋጅ አውጥቶ ወጣቱን በግዳጅ ወደ ጦርነት ግንባር በማፈስ እና ከውጭ አጥፊ ኃይሎች ጋር በመሻረክ የቃላት ጦርነት እና ትንኮሳዎችን ሲፈጽም ቆይቷል።
ሆኖም የጥፋት እና የስግብግብነት አካሄዱ ያስመረረው የትግራይ ሕዝብ ቡድኑን በመግፋቱ ዛሬ ከትግራይ ምድር ከመከላከያ ጎን ሆኖ ቡድኑን እየጠረገ ይገኛል።
የፌዴራል መንግሥት በሕዝቡ ላይ አላስፈላጊ እንግልት እንዳይደርስ በጥንቃቄ እርምጃ ከመውሰዱ ጎን ለጎን፣ በቡድኑ አፍራሽ እንቅስቃሴ ምክንያት ተቋርጠው የነበሩ መሠረታዊ አገልግሎቶችን በፍጥነት የመመለስ ሥራዎችን አጠናክሮ ቀጥሏል።
የቴሌኮም፣ የባንክ እና የኤሌክትሪክ አገልግሎቶች በፍጥነት እንዲጀመሩ እና ሕዝቡ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴው እንዲመለስ ከተደረጉ ሰፊ ጥረቶች ባሻገር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተቋረጠውን ወደ መቐለ ከተማ የሚደረግ የበረራ አገልግሎት ዳግም ጀምሯል።
ይህ የትራንስፖርት መስመር ዳግም መከፈት የክልሉን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትሥሥር ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ነው።
ከመሠረታዊ አገልግሎቶች መመለስ ጎን ለጎን እጅግ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ሌላው ዋና ተግባር የዕለት ደራሽ ዕርዳታዎችን በፍጥነት እና ያለምንም እንቅፋት ለተቸገሩ ወገኖች ማድረስ ነው።
የፌዴራል መንግሥት በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖቻችንን በፍጥነት ለመደገፍ የሚያስችሉ የምግብ፣ የመድኃኒት እና የሕክምና ቁሳቁሶችን በስፋት በማሰራጨት ላይ ይገኛል።
ይህ ፈጣን አገልግሎቶችን የመመለስ እና ሰብዓዊ ዕርዳታ የመስጠት ሂደት መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ ያለውን እውነተኛ የልማት፣ የሰላም እና የመልካም አኗኗር መሻት በግልጽ የሚያሳይ ነው።
የትግራይ ሕዝብ ከአጥፊው ቡድን ተጽዕኖ ተላቅቆ ከወንድም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመተባበር ወደ ፈጣን የልማት እና የዕድገት ምዕራፍ የሚሸጋገርበት ጊዜ አሁን ነው።
#የመደመርመንግሥት
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: